Fana: At a Speed of Life!

ጊዜያዊ ችግሮቻችንን በመረዳዳት እየተሻገርን ለዘላቂ ልማታችን በመስራት የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጊዜያዊ ችግሮቻችንን በመረዳዳት እየተሻገርን ለዘላቂ ልማታችን በመስራት የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ÷ የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ 25ኛውን እና 26ኛውን የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል አገልግሎት ማስጀመራቸውን አስታውቀዋል።

ከ2014 ጀምረን በቀን አንድ ጊዜ እንኳን ምግብ ለማግኘት ለሚቸገሩ ወገኖቻችን 24 የምገባ ማዕከላትን ከፍተን ንፁህ፣ ጤናማ እና ትኩስ ምግብ ለአቅመ ደካሞች፣ ለአካል ጉዳተኞች እና ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ለተጋለጡ ወገኖቻችን እየመገብን መሆናችን ይታወቃል ሲሉም አስታውሰዋል።

የትንሣኤን በዓል ምክንያት በማድረግ በየካ ክፍለ ከተማ ጉራራ አካባቢ 25ኛውን እና በቦሌ ክፍለ ከተማ ቦሌ ሚካኤል አካባቢ ደግሞ 26ኛውን የምገባ ማዕከል ከፍተን አገልግሎት አስጀምረናል ብለዋል።

ዛሬ የተጀመሩ የምገባ ማዕከላት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በመጠለያ ይኖሩ የነበሩ እና ምንም ገቢ የሌላቸው አቅመ ደካሞች እና ለተለያዩ ለማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ወገኖች ያሉበት አካባቢ መሆኑንም አመላክተዋል።

25ኛውን የምገባ ማዕከል የገነቡትን እንዲሁም የምገባውን ወጪ የሚሸፍነውን የአያት አክሲዮን ማህበር እና የኢፌዴሪ የጉምሩክ ኮሚሽን በተጠቃሚዎቹ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ጊዜያዊ ችግሮቻችንን በመረዳዳት እየተሻገርን ለዘላቂ ልማታችን ደግሞ 24/7 በመስራት የኢትዮጵያን ብልጽግና እናረጋግጣለን ሲሉም ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.