የተለወጠችና ከልመና የወጣች ሀገር እውን ከማድረግ ውጪ ሌላ ሃሳብ የለንም – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለወጠችና ከልመና የወጣች ሀገር እውን ከማድረግ ውጪ ሌላ ሃሳብ የለንም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ የትንሳኤ በዓልን በገላን ጉራ ከሚገኙ የካሳንቺስ ልማት ተነሺዎች ጋር አሳልፈናል ብለዋል።
ጎስቋላ የነበረውን ከተማ እንቀይረው ያልነው ለጋራ ጥቅም፣ ለልጆቻችን ደስታ እና መጻኢውን ዘመን ለማሳመር ብቻ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የተለወጠችና ከልመና የወጣች ሀገር እውን ከማድረግ ውጪ ሌላ ሃሳብ የለንም ብለዋል።
ይህ አዲሱ ሰፈራችሁ የምትኖሩበት ነው፤ ቀድሞ የኖራችሁበት ሰፈራችሁን ሄዳችሁ እንድታዩት እጋብዛለሁ በማለት ገልጸው፤ ቃል በገባነው መሰረት ካሳንቺስ እጅግ ውብ ሆኗል ሲሉ ተናግረዋል።
ልጆቻችን ተስፋ አላቸው፣ ከእኛ የተሻለ ህይወት መኖር ይችላሉ ሲሉ አስገንዝበው፤ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ቅርብ ነው፤ እኛም እናያለን፣ ልጆቻችንም ይወርሳሉ ብለዋል።