በሐረሪ ክልል ለብሔራዊ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የምሳ ግብዣ መርሐ-ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሐረሪ ክልል ለሚገኙ ለብሔራዊ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የትንሳዔ በዓልን ምክንያት በማድረግ የምሳ ግብዣ መርሐ-ግብር ተካሂዷል።
በመርሐ-ግብሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ÷ ወጣቶቹ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ በመሳተፍ እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
የብሔራዊ በጎ ፈቃድ ወጣቶች የሚሰጡት አገልግሎት የማህበረሰቡን ችግሮች በማቃለል አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡበት እንደሚገኝ ገልፀዋል።
በተለይ የብሔራዊ በጎ ፈቃድ መርሐ-ግብሩ ቀድሞ የነበረውን እርስ በርስ የመረዳዳት እሴቶችን በማጎልበት አበርክቶው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
ለትንሳዔ በዓል የእንኳን አደረሳቹ መልዕክት በማስተላለፍም÷ በዓሉን በወንድማማችነት መንፈስ በመደጋገፍ ማሳለፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ አመራሮች እና የብሔራዊ በጎ ፈቃድ መርሀ-ግብር ተሳታፊ ወጣቶች መገኘታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡