ኢባትሎ በጅቡቲ ከሚገኙ መርከበኞች ጋር የትንሳዔ በዓልን አከበረ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 12፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ (ኢባትሎ) በጅቡቲ ወደብ ከሚገኙ መርከበኞች ጋር የትንሳዔ በዓልን አከበረ።
ኢትዮጵያዊያኑ ባሕረኞች የኢትዮጵያን የገቢና ወጪ ንግድ ለማሳለጥ በአስቸጋሪ የአየር ጠባይ፣ በረጋውና በሚናወጠው የባሕር ወሽመጥ ለወራት ሌት ተቀን ይተጋሉ ሲል ኢባትሎ ገልጿል።
ባለሙያዎቹ መርከቦቹን ሀገራቸው፤ የመርከቧን ካፕቴኖች መሪያቸው፤ ሰንደቅ ዓላማቸውን ደግሞ መለያቸው በማድረግ በተለያዩ ዓለማት በሚገኙ ውቅያኖሶችና ባሕሮች በዓልን እንደሚያሳልፉ ጠቅሷል።
በአሁኑ የትንሳዔ በዓል በአጋጣሚ የጅቡቲ ወደብ ላይ የሚገኙት የጋምቤላ እና ሰመራ መርከበኞች በዓሉን ማክበር መቻላቸውን ጠቅሶ፤ የተቋሙ ኤም ቲ ኤስ ቅርንጫፍ አመራሮች ከመርከበኞች ጋር በጅቡቲ ወደብ በዓሉን ማክበራቸውን አስታውቋል።
መርከበኞቹ በዓሉን በዚህ መልኩ ማክበራቸው የቤተሰብ ስሜት እንዲሰማቸው ያደረገ መሆኑን መናገራቸውን የኢባትሎ መረጃ አመላክቷል።
መርከበኞች እና የገቢ ወጪ ጭነት እያሳለጡ ለሚገኙ የየብስ ትራንስፖርት የከባድ ጭነት አሽከርካሪዎቻች ዘወትር ሀገራቸውን በማገልገል ላይ እንደሚገኙ የገለጸው ኢባትሎ፤ ሀገር ላቅ ያለ ምስጋና አላት ብሏል።