ቬይትናም ከአፍሪካ ጋር ለሚኖራት ግንኙነት ኢትዮጵያን እንደበር ትጠቀማለች- ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በእስያ ለምትዳርገው ሁለንተናዊ ግንኙነት ቬይትናምን፤ ቬይትናምም በአፍሪካ ለሚኖራት ግንኙነት ኢትዮጵያን እንደ ስልታዊ አጋር ይጠቀማሉ ሲሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሠ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሣምንት በቬይትናም ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አሥመልክቶ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም፤ ቬይትናም ከ1984 ጀምሮ የኢኮኖሚ ሪፎርም ማካሄዷ እና ይህን ተከትሎም በ1990ዎቹ 70 በመቶ የነበረውን የዜጎቿን ድህነት ሙሉ በሙሉ ቀርፋ፤ ዛሬ በዓለም በከፍተኛ ሁኔታ ሩዝ፣ ቡና እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በቅታለች ብለዋል፡፡
በኢንዱስትሪው ዘርፍም ከዓለም የንግድ ድርጅት እና ሌሎች በቀጣናው ከሚገኙ ጋር ባደረገችው ስምምነት ከፍተኛ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳቧን ገልጸው፤ ኤክስፖርት መር ኢኮኖሚ መገንባቷንም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከሀገሪቱ መሪዎች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች፤ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት ከስንዴ ቀጥላ ለሩዝ ከፍተኛ ግምት መስጠቷ ተነስቷል ብለዋል፡፡
ቬይትናም በሩዝ ምርትበጣም ከፍተኛ የሚባል ደረጃ ላይ የደረሰች በመሆኑ፤ ሩዝን ለማስፋፋትና በምግብ ሰብል እራስን ለመቻል በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ ልምድ ማግኘት መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ቡና ምርቶች ልምድ የሚገኝባት ሀገር መሆኗን አንስተዋል፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ እያከናወነች ያለው ተግባር ከቬይትናም ጋር የሚያመሳስለው ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ ከዚህም ልምድ ማግኘት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከኤክስፖርት መር ኢንዱስትሪዋ ጋር በተያያዘም ኤሌክትሮኒክስ፣ ጨርቃጨርቅና ጫማ ምርቶች ከፍተኛውን ቦታ እንደሚይዙ ጠቁመው፤ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ተኪ ምርቶችን ለማምረት እያደረገችው ላለው እንቅስቃሴ ጠቃሚ ልምድ ተገኝቶበታል ነው ያሉት፡፡
ቬይትናም ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በብዛት ያስፋፋች መሆኗን ገልጸው፤ ኢትዮጵያም በዚህ ዘርፍ ከፍተኛ ሥራ እያከናወነች በመሆኑ የቴክኒክ ልምዶችን ለመለዋወጥ የሚያስችል ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
በከተማ ግንባታ፣ በኮሪደር ልማት ሥራ፣ በድህነት ቅነሳ እና በቱሪዝም ዘርፉም ሀገራቱ ልምድ ለመለዋወጥ የሚያስችላቸው ሁኔታ መፈጠሩን አንስተዋል፡፡
በቅርቡ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቬይትናምን ከአፍሪካ ለማገናኘት ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁሉም የሀገሪቱ መሪዎች እና ባለሃብቶች ጋር ባደረጓቸው ውይይቶች መገንዘብ እንደተቻለው፤ ከአፍሪካ ጋር ለመወዳጀት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፤ ባለሃብቶችም በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረግ ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡
በአጠቃላይ በተደረገው ውይይት፤ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በትምህርት አብሮ ለመሥራት እና ኢትዮጵያን የአፍሪካ መግቢያ በር አድርጎ ለመጠቀም ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩ ተንጸባርቋል ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያም በእስያ በምታደርጋቸው ግንኙነቶች ቬይትናምን እንደ ስልታዊ አጋር እንደምትወስድ ተገልጿል ብለዋል በማብራሪያቸው፡፡
በዮሐንስ ደርበው