የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የቬይትናም ጉብኝት በበርካታ ዘርፎች ልምድ የተቀሰመበት ነው – ቢልለኔ ስዩም
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 13፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቬይትናም ጉብኝት የሀገራቱን ግንኙነት የሚያጠናክርና በበርካታ ዘርፎች ልምድ የተቀሰመበት ነው ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ፡፡
ቢልለኔ ስዩም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት በቬይትናም ያደረጉትን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በማብራሪያቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቬይትናም ቆይታቸው ከሀገሪቱ የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር መምከራቸውን ተናግረዋል፡፡
በዚህም በሁለቱ ሀገራት መካከል በተለያዩ ዘርፎች ያለውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር የሚያስችል ውይይት መደረጉን ነው ያስረዱት፡፡
የቬይትናም ጠቅላይ ሚኒስትር ፋም ሚን ቺን በቤተ መንግሥታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ደማቅ አቀባበል እንዳደረጉላቸው አንስተዋል፡፡
በውይይታቸውም በተለይም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ትስስር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በትኩረት መምከራቸውን አንስተዋል፡፡
ቬይትናም በብዛት የምትታወቀው መዋዕለ ንዋይ በመሳብ ነው ያሉት ቢልለኔ ስዩም÷ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ከሀገሪቱ በኢኮኖሚ፣ ኢንዱስትሪ፣ ግብርና እና ሌሎች ዘርፎች ልምድ መቅሰሟን አብራርተዋል፡፡
የቬይትናም ከፍተኛ አመራሮች ጋር በተደረጉ ውይይቶች በኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለውን አስቻይ ሁኔታ በመጠቀም ግንኙነቱን ይበልጥ ማጠናከር እንደሚፈልጉ መናገራቸውን አብራርተዋል፡፡
በተለይም የቬይትናም ባለሃብቶች በኢትጵያ በተለያዩ ዘርፎች መዋዕለ ንዋያቸውን ማፍሰስ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ምክክር መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃኖይ የስማርት ሲቲ ፕሮጀክት ያደጉት ጉብኝትም ኢትዮጵያ እያከናወነችው ከሚገኘው የኮሪደር ልማት ጋር ለማስተሳሰር እና ልምድ ለመቀሰም እድል መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡
ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን በመቀመር በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የዘመናዊ ከተማ ፕሮጀክቶችን ነባራዊ ሁኔታውን በማገናዘብ ጥራቱን የጠበቀ ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፒ4ጂ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የገቡትን ቃል በማክበር ተግባራዊነቱን ማሳደግ እንዳለባቸው አጽንኦት መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየተገበረቻቸው የሚገኙ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ጨምሮ የተለያዩ ኢኒሼቲቮችን በተመለከተ ገለጻ ማድረጋቸውንም አንስተዋል፡፡
በመላኩ ገድፍ