የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላኖች ግዥና መዳረሻዎችን ከማሳደግ አንጻር የተቀመጡ ግቦች ማሳካቱን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአውሮፕላኖች ግዥ እና መዳረሻዎችን ከማሳደግ አንጻር በፈረንጆቹ 2025 የተቀመጡ ግቦች ማሳካቱን የአየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ገለጹ።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ከቢቢሲ “ፎከስ አፍሪካ” ጋር ባደረጉት ቆይታ አየር መንገዱ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ያለውን ጠንካራ ግንኙነት አንስተው÷ በቅርቡ 67 አውሮፕላኖችን መታዘዛቸውንና የተመረጡ አውሮፕላን ክፍሎችን ለቦይንግ በኢትዮጵያ እየተመረቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የትኬት ዋጋ ጭማሪን በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸው በሰጡት ማብራሪያ÷ ከፍተኛ የመሬት አያያዝ ክፍያዎች፣ የነዳጅ ወጪዎች በአፍሪካ ከመካከለኛው ምስራቅ፣ አውሮፓ እና እስያ ጋር ሲነፃፀሩ በጣም ውድ በመሆናቸው እንዲሁም የተለያዩ ግብር በአህጉሪቱ የአውሮፕላን ትራንስፖርት ዋጋ ከፍ እንዲል አስተዋጽዖ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዓመት 110 ሚሊየን መንገደኞች የማስተናገድ አቅም ያለውን አዲስ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ለመገንባት ዝግጅት ላይ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የግንባታው ሂደት ሁለት ምዕራፎች እንደሚኖሩት ገልጸው÷ 60 ሚሊየን መንገደኞችን የሚያስተናግደው የመጀመሪያው ምዕራፍ ግምባታ በፈረንጆቹ 2029 እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል፡፡
አዲሱ የግንባታ ፕሮጀክት በሚከናወንባቸው አካባቢዎች ያሉ ተነሺ አርሶ አደሮችን እና ማህበረሰቡ ኑሯቸውን ለማስቀጠል የሚረዱ መኖሪያ ቤቶችን፣ አዳዲስ ህንጻዎች፣ አግሮ ፕሮሰሲንግ ማዕከላት እና የንግድ ማዕከል በመገንባት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
የአዲሱ አውሮፕላን ማረፊያ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት በመጪው ኅዳር ወር መጨረሻ እንደሚከናወንም አመላክተዋል።
በሔለን ታደሰ