አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ ልማት እና እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ለኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች ላይ የሚያደርገውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ፡፡
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምኅረቱ እና የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከ2025ቱ የዓለም ባንክ ቡድን እና አይ ኤም ኤፍ ስብሰባ ጎን ለጎን ከአይ ኤም ኤፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ማኔጂንግ ዳይሬክተሯ ወይይቱን ተከትሎ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ÷ ከኢትዮጵያ የፋይናንስ ልዑክ ጋር የምስራቅ አፍሪካ ሀገራትን የኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳዎች በተመለከተ ፍሪያማ ውይይት ማድረጋቸው ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት አይ ኤም ኤፍ ለኢትዮጵያ ልማት እና እድገት የሚያደርገውን ድጋፍና አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውንም አመላክተዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ ለስድስት ቀናት በሚካሄደው የ2025ቱ የዓለም ባንክ ቡድን እና አይ ኤም ኤፍ ዓመታዊ ስብሰባ የሁለቱ ተቋማት የጋራ ኮሚቴን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት የፋይናንስ ልዑኮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡