ውስንነቶችን እያሻሻልን ለውጤታማነት እየተጋን ነው- አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል የበጀት ዓመቱ 3ኛ ሩብ ዓመት የመንግሥትና የፓርቲ የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የተመዘገቡ ውጤቶችና የተስተዋሉ ውስንነቶችን በጥልቀት መገምገም በቀጣይ ለምናከናውናቸው ተግባራት ስኬታማነት ይረዳል፡፡
የብልጽግና ጉዞን ለማሳካት የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደው ሲተገበሩ መቆየታቸውን አውስተው፤ አፈጻጸሞችን በአግባቡ በመገምገም ውስንነት ያለባቸውን እያሻሻልን ለውጤታማነት እየተጋን ነው ብለዋል።
በተለይም በ4ኛው ሩብ ዓመት ጠንካራ ሥራ እንደሚጠበቅ እና ይህም ለአዲሱ በጀት ዓመት የሚያዘጋጅ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በመድረኩ ትኩረት የሚደረግባቸው ዋና ዋና ጉዳዮችም፤ የተመዘገበው አፈፃፀም ምን ይመስላል፣ ውጤታማ አፈጻጸሞችን እንዴት አሳካን፣ ያልተሳኩ ዕቅዶችን ለምን መፈጸም አልተቻለም፣ ውስንነቶችን መቅረፍ የሚቻልበትንና የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ እንዴት እያዘጋጀን ነው እና የአመራርነት ዐቅማችን ምን ያህል ነው የሚሉት መሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
በታምራት ደለሊ