ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሀገሪቱ አካባቢዎች ቀጣይነት እንደሚኖረው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሚቀጥሉት 10 ቀናት ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛዎቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ አካባቢዎች ቀጣይነት እንደሚኖረው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስትቲዩት አስታወቀ፡፡
ኢንስትቲዩቱ ከሚያዝያ 13 እስከ 22/2017 ዓ.ም የሚኖረውን የአየር ሁኔታ ትንበያ ይፋ ባደረገበት መረጃ÷ በሚቀጥሉት አሥር ቀናት ዝናብ ሰጭ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛዎቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ቀጣይነት የሚኖራቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡
ይሁን አንጂ አልፎ አልፎ ባሉት ቀናት ደረቅ የአየር ሁኔታዎች እንደሚኖሩም ጠቁመዋል፡፡
በተያያዘ መረጃ በደቡብ፤ በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በምስራቅ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ የደመና ሽፋን ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡
በመሆኑም በበልግ አብቃይ አካባቢዎች በርካታ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ቀላል መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ መባሉን ከኢንስትቲዩቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡