“የአሮን ራምሴ እርግማን “
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዌልሳዊው ኢንተርናሽናል የአርሰናል የቀድሞ አማካኝ ተጫዋች አሮን ራምሴ ግብ በሚያስቆጥርባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ አንድ የዓለማችን ገናና ሰው በሠዓታት ልዩነት ሕይዎቱ ያልፋል፡፡
ይህን አጋጣሚ በተደጋጋሚ ያስተዋሉ ጋዜጠኞችም፤ “የአሮን ራምሴ እርግማን (ዘ ከርስ ኦፍ አሮን ራምሴ)” ሲሉ ይጠሩታል፡፡
አሮን ራምሴ ግብ ባስቆጠረ በሠዓታት ልዩነት ሕይዎታቸውን ካጡ ዝነኞች መካከልም፤ ኦሳማ ቢላደን፣ ሞዐመር ጋዳፊ፣ የአፕል መሥራች እና ባለቤት ስቲቭ ጆብስ፣ የፖፕ ሙዚቃ ስልት አቀንቃኟ ዊትኒ ሂዩስተን፣ ዝነኛው ተዋናይ ሮቢ ዊሊያምስ፣ ፖል ዎከር፣ አለን ሪክማን እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በእንግሊዝ በሻምፒየን ሺፕ እየተሳተፈ ለሚገኘው ካርዲፍ ሲቲ የሚጫወተው አሮን ራምሴ፤ ክለቡ አሰልጣኙን ማሰናበቱን ተከትሎ ከሰሞኑ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ሆኖ በተሾመ በሠዓታት ልዩነት የሮማው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ከዚህ ዓለም ድካም ማረፋቸው አጋጣሚውን አነጋጋሪ አድርጓል፡፡
በተለይም በአርሴናል ቤት በነበረው ቆይታ ግብ ባስቆጠረ ቁጥር፤ “ቀጣዩ ተረኛ ሟች ማን ይሆን” በሚል መነጋገሪያ እንደነበር በርካቶች ያነሳሉ፡፡
በፈረንጆቹ 2008 ለዌልስ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገው አሮን ራምሴ፤ በ20016 የአውሮፓ ዋንጫ ሀገሩን ግማሽ ፍጻሜ ያደረሰበት አጋጣሚ ትልቁ ስኬቱ እንደሆነ ይነገራል፡፡
የዌልስ ብሔራዊ ቡድን አምበል ራምሴ በእግር ኳስ ሕይዎቱ ለካርዲፍ ሲቲ፣ አርሰናል፣ ጁቬንቱስ እና ለፈረንሳዩ ኒስ መጫዎቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በዚህም ከአርሰናል ጋር ሦስት የኤፍ ኤ ዋንጫን ማንሳቱ እና በፈረንጆቹ 2019 ወደ ጁቬንቱስ በሄደበት የመጀመሪያ ዓመት የሴሪኤውን ዋንጫ ከፍ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
በፈረንጆቹ 2022 ከጣሊያኑ ጁቬንቱስ ወደ ፈረንሳዩ ኒስ ያመራው አሮን ራምሴ፤ ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ በፈረንጆቹ 2023 የልጅነት ክለቡን ካርዲፍ ሲቲን ተቀላቅሏል፤ አሁንም በዚሁ ክለብ ይገኛል፡፡
ባሳለፍነው ቅዳሜ ካርዲፍ ሲቲ በሼፊልድ ዩናይትድ 2 ለ 0 መሸነፉን ተከትሎ፤ ክለቡ አሰልጣኝ ኦመር ሪዛን ከኃላፊነት አሰናብቷል፡፡ ይህን ተከትሎም ካርዲፍ ሲቲ የ34 ዓመቱን ተጫዋቹን አሮን ራምሴን በጊዜያዊነት አሰልጣኝ አድርጎ ሾሟል፡፡
ወደ ዲቪዚዮን የመውረድ ሥጋት ያለበት ካርዲፍ ሲቲ፤ በቀሪ ሦስት የሻምፒየን ሺፑ የጨዋታ መርሐ-ግብሮች አሮን ራምሴ ክለቡን እንዲታደግ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎበታል፡፡
በአቤል ንዋይ