የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውጤታማነት ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት እንደሚገባ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውጤታማነት ለማሳደግ ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት እንደሚገባ ተገልጿል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ሐና አርዓያስላሴ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች ጋር የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውጤታማነትን ለማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት÷ ባለፉት ዓመታት በጋራ በተከናወኑ የወንጀል ምርመራ፣ ክስና ክርክር ተግባራት አጥፊዎችን ተጠያቂ ከማድረግ ረገድ አመርቂ ውጤቶች መገኘታቸው ተገልጿል።
በተሰሩ ስራዎች የታዩ ጥንካሬዎችን አጠንክሮ ማስቀጠል ውስንነቶችን በመቅረፍ ጠንካራ የወንጀል ፍትህ አስተዳደር ስርዓት ለመገንባት በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ተነስቷል፡፡
የሥራ ኃላፊዎቹ የጋራ የአሰራር ሥርዓት መዘርጋት፣ የወንጀል መረጃ ሥርዓት ማዘመን፣ የምርመራ ስራዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስደገፍ፣ የጋራ ዕቅድ ክትትልና ግምገማ ሥርዓት መዘርጋት እንዲሁም በየደረጃው ቅንጅታዊ አሠራርን ለማጠናከር መግባባታቸው ተጠቁሟል።
በውይይቱ ላይ የተቋማት አመራሮች መገኘታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።