Fana: At a Speed of Life!

አቶ ኦርዲን በድሪ የዜጎችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማረጋገጥ እንደሚሠራ ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዜጎችን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ በትኩረት እንደሚሠራ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

በሐረሪ ክልል የሴክተር መሥሪያ ቤቶች በበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ እየተካሄደ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት በኢኮኖሚ ልማት ዘርፎች የተከናወኑ ተግባራት ቀርበው ግምገማ ተደርጓል፡፡

አቶ ኦርዲን በዚሁ ወቅት ገቢን በተገቢው መንገድ ሰብስቦ ለማኅበራዊና ኢኮኖሚ ልማቶች በማዋል ማሕበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚገባ  አስገንዝበው፤ በገቢ አሰባሰብ ሂደት ላይ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን መቅረፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ፀጋዎችን በአግባቡ አልምቶ በመጠቀም ገቢ ማመንጨት እና ሀብት መፍጠር እንደሚገባ ማስረዳታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

በተከናወኑ ተግባራት የዋጋ ንረትን በማረጋጋት አበረታች ውጤት መመዝገቡን ጠቁመው፤ ይህም አርሶ አደሩ እራሱን በምግብ ከመቻል አልፎ ምርቱን ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን አድርጓል ብለዋል፡፡

በክልሉ የኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሻለ መነቃቃት አለ ያሉት አቶ ኦርዲን፤ በዘርፉ የተሰማሩ አልሚዎች በጊዜ ወደ ሥራ እንዲገቡ የተጀመረው ድጋፍና ክትትል ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል፡፡

ከካፒታል ፕሮጀክቶች አፈፃፀም ጋር በተገናኘም አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸው፤ በተያዘላቸው ጊዜ ያልተከናወኑ ቀሪ ፕሮጀክቶችን በመፈተሽ የእርምት እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቀዋል፡፡

በግምገማው የተገኙ ግብዓቶችን መነሻ ያደረገ የማካካሻ ዕቅድ በማዘጋጀት በዕቅድ ተይዘው ሳይከናወኑ የቀሩ ተግባራትን በቀሪ ጊዜያት ማከናወን እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.