Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ በወሰደችው የአየር ጥቃት ከ500 በላይ የሁቲ አማፂያን መገደላቸው ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) አሜሪካ በየመን በሚንቀሳቀሱ የሁቲ አማጺያን ላይ በፈፀመችው የአየር ጥቃት የአማፂያኑ አዛዦችን ጨምሮ ከ500 በላይ ተዋጊዎች መሞታቸው ተገለፀ፡፡

የሰነዓ ኢንፎርሜሽን ማዕከልን ጠቅሶ አል አራቢያ እንደዘገበው÷የአሜሪካ አየር ሀይል ለሳምንታት በአማፂያኑ ይዞታዎች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃቶችን ፈፅሟል፡፡

የአማፂያኑ የማዘዣ እና የቁጥጥር ማዕከሎች፣ የስልጠና ካምፖች፣ የጦር መሳሪያ ዲፖዎች፣ የመገናኛ ተቋማት እና ሌሎች ወታደራዊ መሰረት ልማቶች በጥቃቱ ዒላማ መሆናቸው ነው የተገለፀው፡፡

ጥቃቱ መሰረተ ልማት ከማውደም በተጨማሪ ከ500 በላይ የአማጺ ቡድኑ አባላት እና ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች መደምሰሳቸው ተመላክቷል፡፡

የየመን የማስታወቂያ ሚኒስትር ሞአማር አል ኤሪያኒ÷ አማፂያኑ የሚፈፅሙት የመርከብ ጥቃትም ሆነ አሜሪካ በሰነዓ የወሰደችው የአየር ጥቃት የየመን መንግስትን እንደማይመለከት ገልፀዋል፡፡

በኢራን ይደገፋሉ የሚባሉት አማፂያኑ የሚፈፅሙት ጥቃት ለቀጣናው የበላይነት የሚደረግ የዓለም ስርዓት ጦርነት ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷በአሜሪካ እና በአማፂያኑ መካከል ያለው ግጭት እና የአፀፋ ጥቃት በቀጣናውን ውጥረት ማስከተሉን ተናግረዋል።

የአሜሪካ ርምጃ የአማፂያኑን ወታደራዊ አቅም የሚያዳክም መሆኑ ተገልጿል፡፡

ዶናልድ ትራምፕ በአማፂያኑ ላይ ዘመቻ እንዲደረግ በመካከለኛው ምስራቅ ለሚገኘው የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ትዕዛዝ ከሰጡ ጀምሮ በተወሰደው ጥቃት ቡድኑ የመከላከል አቅሙ በእጅጉ ተዳክሟል ተብሏል፡፡

በዚህም በቀይ ባሕር እና ባብ ኤል መንዳብ ሰርጥ የሚፈፅሙት ጥቃት ቀንሷል መባሉን አል አራቢያ ኒውስ ዘግቧል፡፡

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.