Fana: At a Speed of Life!

ቦይንግ የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ ከፈተ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ቦይንግ ኩባንያ የአፍሪካ ቢሮውን በአዲስ አበባ መክፈቱ ተገልጿል።

በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)÷ የቢሮው መከፈት የኢትዮጵያን የተሳሰረችና የበለፀገች አፍሪካን እውን የማድረግ ዓለም አቀፋዊ ራዕይ ለማሳካት የሚያግዝ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በብሔራዊ ትራንስፖርት ካውንስል የሚመራ የዘርፉን መሠረተ-ልማት ለማዘመን፣ የትራንስፖርት ንግድ ወጪን ለመቀነስ እና አፍሪካን ለማስተሳሰር የሚያስችል የአስርት ዓመታት ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት እየሰራች መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም በባቡር፣ በወደብ ልማት፣ በአቪዬሽን እና በስማርት ሎጂስቲክስ ዘርፍ እንደ ቦይንግ ካሉ የግል ዘርፎች ጋር በጋራ ለመስራት የ74 ቢሊየን ዶላር የኢንቨስትመንት እቅድ መቀመጡን ጠቁመዋል።

የቦይንግ ኩባንያ አመራር በኢትዮጵያ ላይ ላሳደረው እምነት ምስጋና አቅርበው÷ ይህንን አጋርነት የአውሮፕላን ክፍሎችን በማምረት፣ ስልጠናዎችን በመስጠትና በዘላቂ የአቪዬሽን ነዳጅ ላይ በትብብር በመስራት አጋርነታችንን እናሳድጋለን ብለዋል፡፡

በጋራ ሆነን የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ ዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት መሪነት ከፍ ማድረግ እና አዲስ አበባን የአፍሪካ የኤሮስፔስ ፈጠራ ማዕከል ማድረግ እንችላለን ሲሉም አመላክተዋል።

የቦይንግን የአፍሪካ ቢሮ በአዲስ አበባ መከፈቱ የኢትዮጵያ ሰማይ ድንበር ሳይሆን መግቢያ በር መሆኑ ማሳያ እንደሆነና ለኢኮኖሚ ነፃነት፣ ለአህጉራዊ አንድነት፣ ለዓለም አቀፋዊ አቪዬሽን እድገት አፍሪካ ድርሻዋን እንድትወጣ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ የቦይንግ የመካከለኛው ምስራቅ፣ ቱርክ፣ አፍሪካ እና ማዕከላዊ ኤዥያ ፕሬዚዳንት ኩልጅት ጋታ እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የኩባንያው አመራሮች መገኘታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.