የፓኪስታን ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፓኪስታን መልህቅ ባለሀብቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
በፓኪስታን የሲያልኮት ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት በተዘጋጀው የቢዝነስ ፎረም ላይ በሀገሪቱ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) በአዲስ አበባ በሚካሄደው “Invest Ethiopia” ከፍተኛ ደረጃ የቢዝነስ ፎረም እና የፓኪስታን የነጠላ ሀገር ዐውደ ርዕይ ላይ ባለሃብቶች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነትን ለማጠናከር የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚያከናወኑ ተግባራት ለግዙፎቹ የሲያልኮት ኢንዱስትሪዎች ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ያለመ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የሁለት ዙር የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረጉንም አመላክተዋል።
በመዲናዋ የሚካሄዱት ሁነቶች ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት የሚያሳዩ እና ከፓኪስታን ጋር እያደገ የመጣውን የንግድና ኢንቨስትመንት ብሎም ሁሉን አቀፍ ትብብር አመላካች መሆኑን ጠቅሰዋል።
ሁነቶቹ ፓኪስታናውያን ከኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ከአፍሪካ ባለሃብቶች እና ባለድርሻ አካላት ጋር አጋርነት ለመፍጠር ወርቃማ እድል እንደሆነም ገልጸዋል።
የሲያልኮት ንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ኢክራም ኧል ሀቅ በበኩላቸው÷ አምባሳደሩ በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አድንቀዋል።
የንግድ ምክር ቤቱ አባላት በኢትዮጵያ ያሉትን ልዩ የንግድ እና የኢንቨስትመንት እድሎች ቀርበው ለመፈተሽ የንግድ ሁነቶቹ ላይ እንዲሣተፉም አሳስበዋል።