Fana: At a Speed of Life!

ካዛንቺስ ዛሬ የጋራ ጥረት እና ለውጥ ሽልማታችን ሆኖ ተገኝቷል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 14፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተጎሳቆሉ እና በእጅጉ የተጎዱ ቤቶች እና ከባቢ መገኛ የነበረው ካዛንቺስ ዛሬ የጋራ ጥረት እና ለውጥ ሽልማታችን ሆኖ ተገኝቷል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት የካዛንቺስን የኮሪደር ልማት በይፋ መርቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት÷ ከተሞቻችንን የማዘመን ሰፊ ጥረት አይነተኛ ማሳያ የሆነውን በካዛንቺስ ያለውን የኮሪደር ልማት ክፍል በይፋ መርቀናል ብለዋል።

ከዚሁ አካባቢ ተነስተው ለማኅበረሰባችን የከበረ የኑሮ ሁኔታን ለመፍጠር ያለንን ፅኑ እምነት እና ተግባር በሚያሳይ አኳኋን ለኑሮ ወደ ተሻለ ከባቢ የተዛወሩትን ነዋሪዎች ከጥቂት ቀናት በፊት ጎብኝተን ነበር ሲሉም አክለዋል፡፡

የተዛወሩበት ከባቢ እጅግ ምቹ መሆኑን ማየታቸውን እና ዛሬ ደግሞ የተነሱበትን ሰፈር ድንቅ የኮሪደር ልማት ሥራ መመረቃቸውን ገልጸዋል።

በአስደናቂ አጭር ጊዜ የተጠናቀቀው የካዛንቺስ ለውጥ ለዘመነ ከተማ ልማት ሥራችን ለአረንጓዴ፣ ንፁህ እና ዘመናዊ የከተማ ማዕከላት ያለንን ርዕይ ግዘፍ ነስቶ በማሳየት መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

በዚህ ግዝፈት የሚከወኑ ሥራዎች ሰፋ ያለ ጥረት ይሻሉ፤ ጊዜያዊ ምቾት የሚነሱ ፈተናዎችንም ሊያስከትሉ ይችላሉ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)÷ ነገር ግን ለታላቁ የሀገር ጥቅም የሚከፈሉ አስፈላጊ መስዋዕትነቶች ናቸው ሲሉ ጠቁመዋል።

ይኽ የእድገት መንገድ መቀጠል ያለበት ነው፤ የታደሰ ተስፋ ይሰጣልና፤ በተለይ ለልጆቻችን ነገ ሲሉም አስገንዝበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.