የካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ሥራ እንዲሳካ ላደረጉ አካላት እውቅና ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ሥራ በታሰበው ልክ ስኬታማ እንዲሆን ለታተሩ አካላት ዕውቅና ሰጡ፡፡
ዕውቅናው የተሰጠው፤ ለኮሪደር ልማቱ በሙሉ ፈቃደኝነት በገንዘብና በዓይነት አስተዋጽኦ ላበረከቱ እንዲሁም መንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት እንዲወጣ ላስቻሉ አካላት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህ መሰረትም ባለሃብቶች፣ ኮንትራክተሮች፣ አማካሪዎች እንዲሁም አመራሮች ዕውቅናና ምሥጋና ተችሯቸዋል፡፡
መዲናዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ዘመናዊ ከተማ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከንቲባዋ አረጋግጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካዛንቺስ የኮሪደር ልማትን ትናንት በይፋ መመረቃቸው ይታወቃል፡፡
በካዛንቺስ የኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ሥራ 40 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ 81 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ እና 20 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መስመር ተገንብቷል።
የሕጻናት መጫወቻ ቦታዎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች፣ የሕዝብ መዝናኛ ፕላዛዎች እና አረንጓዴ ፓርኮች፣ ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶች፣ የንግድ ሱቆች እንዲሁም የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችም ተገንብተዋል፡፡
በግዛቸው ግርማዬ