በአጋሮ በከተማ ግብርና እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ውጤታማ መሆናቸው ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 15፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል አጋሮ ከተማ በከተማ ግብርና እየተሠሩ ባሉ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን የከተማዋ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቦርቶላ ዓለማየሁ ገለጹ፡፡
ኃላፊው ከፋና ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ በከተማዋ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ፓፓያ፣ በቆሎ እና የማር ምርት በኩታገጠም በስፋት እየለማ ነው፡፡
የከተማ ግብርና ከሦስት ዓመታት ወዲህ እየተስፋፋ እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነቱ ማደጉን ጠቁመው፤ በተለይም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ለሚገኙ ወገኖች ትልቅ በረከት አስገኝቷል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ለከተማው ነዋሪዎችም ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ተጠቃሚ ማድረጉን ነው ያነሱት፡፡
ከግብርና ጽሕፈት ቤት ጋር በመሆን ቤት ለቤት ጭምር የተሠራው ሥራ ለተገኘው ውጤት ከፍተኛ ሚና ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡
ማሕበረሰቡ ባለው አነስተኛ ቦታ፤ ጥቅል ጎመን፣ ሰላጣ እና ሌሎች አትክልቶችን በማምረት እራሱን ተጠቃሚ ማድረጉን አውስተው፤ በቀጣዩ ክረምት አረንጓዴ ዐሻራን ጨምሮ ልዩ ልዩ የሻይ ቅጠሎችን፣ አቮካዶና የመሳሰሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በኩታገጠም ለማልማት ዝግጅት መጠናቀቁን አረጋግጠዋል፡፡
በአቤል ንዋይ