የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የኮሪደርና ሌሎች የልማት ስራዎችን እየጎበኙ ነው
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የፌደራል መንግሥት ተቋማት የኢኮኖሚ ዘርፍ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።
የሥራ ኃላፊዎቹ መነሻቸውን ካዛንችስ ኮሪደር ልማት በማድረግ በተለያዩ የመዲናዋ አካባቢዎች የተከናወኑ የልማት ስራዎችን ተዘዋውረው እንደሚጎበኙም ተገልጿል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀኃይ ጳውሎስ ጉብኝቱን አስመልክቶ ባደረጉት ገለፃ÷ ጉብኝቱ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተመዘገቡ የሚገኙ ስኬቶችን በተግባር እንዲመለከቱ ለማስቻል ያለመ ነው ብለዋል።
እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች የቀጣዩን ትውልድ መፂኢ እጣ ፋንታ ታሳቢ በማድረግ ተሻጋሪ እሳቤ ተግባራዊ የተደረገባቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ በበኩላቸው÷ በመዲናዋ የተከናወኑ የኮሪደርና መልሶ ማልማት ስራዎች የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከማሳደግ ባለፈ በተጎሳቆለ ሁኔታ ይኖሩ የነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ኑሮ የቀየረ ነው ብለዋል።
በሂደቱም ቅርሶችን በመጠበቅ ለትውልድ የሚሻገሩ ስኬታማ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች የተከናወኑበት መሆኑን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።