Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑ ተገልጿል።

የኦሮሚያ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ሶስተኛ ጉባዔ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት እየተካሄደ ይገኛል።

በጉባዔው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ አቶ ሽማልስ አብዲሳ፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) እና ሌሎች የፌዴራል እና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።

በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የኦሮሚያ ክልል የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ በወቅቱ እንደተናገሩት÷ በክልሉ ግብርናውን ከተለመደው አሰራር በማላቀቅ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው።

ይህንኑ ሒደት ለማሳለጥ የተቋቋመው ምክር ቤቱ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን የሚያግዙ የማማከር፣ የማስተባበርና ችግሮችን የመለየት ብሎም የመፍትሄ አቅጣጫ የማስቀመጥ ስራ እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ምክር ቤቱ ከተቋቋመ ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ የተሰሩ ሥራዎች የገጠር ልማት ግቦችን ከማሳካት አንፃር ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን አንስተዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በግብርና ላይ የተከናወነው የሽግግር ሥራ ቀደም ሲል ከውጪ ሲገባ የነበረውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ማምረት ማስቻሉን አስታውሰዋል።

በክልሉ ግብርናውን በማዘመን ረገድም ትልቅ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ጠቁመው÷ በክልሉ በትራክተር የሚታረስ መሬት ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ ጨምሯል ብለዋል።

ግብርናው እየዘመነ በመምጣቱም ወጣቶች የግብርና ሥራ ላይ ያላቸው ተሳትፎ እንዲያድግ እድል መፍጠሩን ነው ያስረዱት፡፡

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸው÷ በክልሉ እየታየ ያለውን ለውጥ ለማሳካት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤቱ ትልቅ ስራ እየሰራ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በመድረኩ እስካሁን የተገኙ ውጤቶችን የማጠናከር እና ቀሪ ግቦችን ለማሳካት በሚደረጉ ሥራዎች ላይ በጥልቀት ውይይት እንደሚደረግ ተመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.