ብልጽግና ፓርቲ የልማት ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ በመፈፀም ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል – አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ መደበኛ ስራዎችን፣ የንቅናቄ ተግባራትን፣ የፖለቲካ፣ የፀጥታ እና የልማት ሥራዎችን በተቀናጀ መልኩ በመፈፀም ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሉን የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
አቶ አደም ፋራህ በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው÷የብልፅግና ፓርቲ የዘጠኝ ወራት የፓርቲ ሥራዎች አፈፃፀም የተቋሙ የዘርፍ ኃላፊዎች፣ የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ሌሎች የፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አመራሮች በተገኙበት ዛሬ መገምገማቸውን አስታውቀዋል።
በ2017 በጀት ዓመት የፓርቲ ሥራዎቻችን ብልፅግና በቁሳዊና ሰብዓዊ ሀብት አቅሙ የተጠናከረ፣ በዘመናዊ መረጃና በአሰራር ሥርዓቱ የደረጀ፣ የተደራጀ፣ የተዋሐደ፣ የተጽእኖ አቅሙ የዳበረና እንደ ሀገር የትርክት የበላይነትና ቅቡልነትን ያረጋገጠ ፓርቲ እንዲሆን ማስቻልን እንደ ዋና ዓላማ በመያዝ ስንሰራ ቆይተናል ብለዋል።
በዚሁ መሰረት በ3ኛ ሩብ ዓመት አፈፃፀማችን ለጋራ ዓላማ እና ተልእኮ በእሳቤዎቻችን ላይ ፀንተን በመቆም በፓርቲ መደበኛ ስራዎች፣ በንቅናቄ ተግባራት፣ የፖለቲካ፣ የፀጥታ እና የልማት ስራዎችን በተቀናጀ መልኩ በመፈፀም ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏልም ነው ያሉት።
በተለይም በአበይት ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ ከፓርቲው አመራር፣ አባላት እና ከልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይነት ያላቸው ውይይቶችን በማድረግ በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች መግባባት ለመፍጠር ካደረግነው ጥረት ባሻገር ከመድረኮቹ የመፍትሄ ሀሳቦችን እና ገንቢ ግብዓቶችን በመቃረም በተከተልነው አቅጣጫ ስኬታማ ስራዎችን መስራት የቻልንባቸው እድሎች ተፈጥረዋል ሲሉ አክለዋል።
ተቋማዊ አቅማችንን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስም ፓርቲው በአሰራር ስርዓቶች በማጠናከር፣ አደረጃጀቶቻችንን ተልእኳቸውን በብቃት የመፈፀም አቅም በማጎልበት፣ ቀጣይነት ባለው መልኩ የአመራርና አባላት አቅም በመገንባት፣ የአመራር ምዘና እና የማስተካከያ የእርምት ርምጃዎችን በመውሰድ እንዲሁም የአመራርና የአባላት የተግባር አፈፃፀም በማሻሻል ረገድ ተጨባጭ ስኬቶችን አስመዝግበናል ብለዋል።
የወጣት እና የሴት ክንፍ መዋቅሮቻችንን በማጠናከር፣ በሀገር ውስጥ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በትብብር በመስራት እንዲሁም ከውጭ እህት ፓርቲዎች ጋር መርህን በጠበቀ አኳኃን ብሄራዊ ጥቅሞችን እና ክብርን በሚያስጠብቅ መልኩ ለጋራ አላማ በጋራ በመስራት ረገድ የተሰሩ ስራዎች ፍሬያማ እንደነበሩም አመላክተዋል።
በአብይት ፓርቲያዊ ኩነቶች አፈፃፀም ላይም የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በስኬት እንዲጠናቀቅ እና የፓርቲውን 5ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በሰብዓዊነት እና በሰው ተኮር እሳቤዎች ደምቆ እንዲከበር በማድረግ ተጨባጭ ፖለቲካዊ ውጤቶች መመዝገቡን ገልጸዋል።
በቀጣይም ቀሪ የበጀት ዓመቱን ሥራዎችን በተናበበ፣ በተቀናጀና በተሟላ መልኩ በጥራት መፈፀም፣ በየደረጃው የሚካሄዱ ውይይቶችና ግምገማዎች ችግር ፈቺ እንዲሆኑ ማድረግና የአባላት የምልመላ ጥራት ማረጋገጥ ሥራዎች እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።
የፓርቲ አደረጃጀቶች ተልዕኳቸውን በብቃት እንዲወጡ ማድረግ፣ የተግባር አፈፃፀም ውጤታማነት እና የሥነ ምግባር ችግር ያለባቸው አመራርና አባላት የማጥራት ሥራ መስራት እና ሁሉንም አማራጮች በመጠቀም ውጤታማ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ሥራዎችን የምንሰራ ይሆናል ሲሉም አብራርተዋል።