Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ስኬት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሞክሮ የሚሆን ነው – ሞሰስ ቪላካቲ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ከአፍሪካ ህብረት የግብርና እና ገጠር ልማት ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች እንደምትገኝ አስረድተዋል፡፡

በተለይም በስንዴ ልማት፣ በሌማት ትሩፋት እንዲሁም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አመርቂ ስኬቶች መመዝገባቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የተመዘገቡ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ለማካፈል ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

አፍሪካ በግብርናው ዘርፍ ያላትን የመልማት አቅም በመጠቀም የምግብ ዋስትናን እና የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኮሚሽነር ሞሰስ ቪላካቲን በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበች ያለው ውጤት ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንደጥሩ ተሞክሮ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአፍሪካን የምግብ ዋስትና እና የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ በዘርፉ የልምድ ልውውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአፈር ማዳበሪያ፣ በምርጥ ዘር ብዜት፣ በግብርና ዲጂታላይዜሽን እንዲሁም በአፈር ካርታ ሥራ ላይ በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ መናገራቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.