ምክር ቤቱ የክልሉ ግብርና ሽግግር ሒደት እንዲፋጠን እያገዘ ነው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 16፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኦሮሚያ ክልል የግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት የክልሉ የግብርና ሽግግር ሒደት እንዲፋጠን የተሻለ እገዛ እያደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።
በኦሮሚያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት 3ኛ ጉባዔ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተሳተፉበት ተካሄዷል።
በጉባዔው ላይ የተገኙት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፥ የግብርና ዘርፉ ከፍተኛ ውጤት እየተገኘበት መሆኑን ተናግረዋል።
በእስካሁኑ ሒደት ከፍተኛ ውጤት እየተገኘበት ያለውን የግብርና ዘርፍ የበለጠ ለማሳደግና ለማስፋፋት ምክር ቤቱ በጎ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
የኦሮሚያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ከተመሰረተ ጀምሮ በጥናት ላይ ተመርኩዞ ባከናወነው ሥራ ጥሩ ውጤት እየተገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
ምክር ቤቱ የክልሉ መንግስት የሚፈልገውን ያህል ውጤታማ እንዲሆን የጀመረውን ሥራ እንዲያጠናክር ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
ከዚህም ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ በግብርና ኤክስቴንሽን የተጋዙ አዳዲስ ኢንሼቲቮች በመንደፍ የግብርናውን ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ መስራት እንደሚገባም አስረድተዋል።
የአርሶ አደሩን ግንዛቤና ዕውቀት የሚያሳድጉ፣ምርታማነትን የሚጨምሩ፣ የገበያ ትስስር ችግሮችን የሚፈቱ የጥናትና ምርምር ሥራዎችንም በትኩረት እንዲያከናወኑ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የምክር ቤቱ ጥረት እንዲሳካ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ክላስተሮች የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡም አቶ ሽመልስ አስገንዝበዋል።
የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ የኦሮሚያ ክልል በግብርናው ዘርፍ እያስመዘገበ ያለው ሽግግር ለሌሎች ክልሎችም ልምድ የሚሆን ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የምክር ቤቱን ዓላማ የበለጠ ለማሳካት ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት ተልዕኳቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ሚኒስትሩ አሳስበዋል።