በዜጎች ላይ እገታና ግድያ እየፈጸመ ባለው ፅንፈኛ ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዜጎች ላይ እገታና ግድያ በመፈፀም የትምህርት ሂደትን በማወክ በመምህራን ላይ በደልና ግፍ እያደረሰ ባለው ፅንፈኛ ቡድን ላይ የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የአማራ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ አስታወቀ፡፡
በክልሉ ያለውን አጠቃላይ የፀጥታ ሁኔታና በፅንፈኛው ቡድን ላይ እየተወሰደ ያለውን ሕግ የማስከበር እርምጃ በተመለከተ የቢሮው ኃላፊ እሸቴ የሱፍ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ሀገር የማፍረስ ዓላማ ይዞ የተነሳው ፅንፈኛ ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በሰዎች ላይ ግድያ፣ ዘረፋና ውድመት አስከትሏል፡፡
ከዚህ ተግባር በመታቀብ ሰላማዊ አማራጭን በመከተል የጥፋት መንገዱን እንዲተው በመንግስት ተደጋጋሚ ጥሪ መቅረቡንና አሁንም የሰላም እጁን እንዳላጠፈ ገልፀዋል።
በዚህም በርካታ ታጣቂዎች የፅንፈኛ ቡድኑን እኩይ አላማ በቅጡ በመረዳትና የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለስ መቻላቸውን አውስተዋል፡፡
ከዚህ ውጭ በጥፋት መንገድ በመቀጠል በግድያ፣ ዘረፋና የእገታ ተግባር ላይ በሚገኘው ፅንፈኛ ቡድን ላይ የተቀናጀና የተጠናከረ ሕግ የማስከበር እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።
ፅንፈኛ ቡድኑ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ መንገድ በመዝጋት የማዳበሪያ አቅርቦትና ሌሎችም ማህበራዊ አገልግሎቶችን ከማስተጓጎል ባለፈ አርሶ አደሮች እንዳይሰሩና ምርታቸውን ለገበያ እንዳያቀርቡ ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
የሐይማኖት አባቶችንና የሀገር ሽማግሌዎችን ጭምር በመግደልና በማገት ግፍ ሲፈፅም መቆየቱንም ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡
በተለይም በትምህርት ቤቶች ላይ ቦንብ በመጣል፣ መምህራንን በማሰርና በመግደል እንዲሁም ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ በመከልከል ፀረ-ሕዝብ መሆኑን በተግባር አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
በመሆኑም በዚህ የሀገርና የሕዝብ ፀር በሆነ ፅንፈኛ ስብስብ ላይ በጥብቅ ክትትል የማያዳግም እርምጃ እየተወሰደበት ነው ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡
በዚህም እየተበታተነ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰዎችን ለመዝረፍና ለማገት እየሞከረ ነው፤ በሕዝቡ ጥቆማ የፀጥታ ኃይሉ ተከታትሎ እርምጃ እየወሰደበት ይገኛል ብለዋል።
ይህን ተከትሎም በብዙ አካባቢዎች ሰላም እየተፈጠረ የማዳበሪያና ሌሎች የግብርና ግብዓቶች ለአርሶ አደሮች እየቀረቡ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
በሁሉም አካባቢዎች በሚደረገው የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴ የሕዝቡ እገዛ፣ ድጋፍና ትብብር ተጠናክሮ መቀጠሉንም አንስተዋል።