Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ማዳበሪያ ለዩኒየኖችና ማኅበራት ደረሰ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለ2017/18 የመኸር ወቅት የሚውል 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዩኒየኖችና ማኅበራት መድረሱን የኦሮሚያ ክልል ኅብረት ሥራ ማስፋፈያ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ማዳበሪያው በጊዜ በመድረሱ ሥርጭቱም በአግባቡ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት የኤጀንሲው ምክትል ኃላፊ ሂንሴኔ ሙሐመድ፤ አቅርቦቱ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ2 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ዘንድሮ 10 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለማቅረብ መታቀዱን አውስተው፤ ዩኒየኖችና ማኅበራት ጋር ከደረሰው 5 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል መካከል ከ800 ሺህ ኩንታል የሚልቀው ለአርሶ አደሩ ተሰራጭቷል ብለዋል፡፡

የመኸር ወቅት ቀድሞ በሚጀምርባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ በመስጠት የማዳበሪያ ሥርጭቱ እየተከናወነ መሆኑን እና ሙሉ በሙሉ ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ከባለድርሻ አካላት ጋር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የግብይት ሂደቱ በዲጂታል መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ያነሱት ምክትል ኃላፊዋ፤ ይህም ሕገ-ወጥ የማዳበሪያ ሥርጭትን ለመከላከል ማገዙን ለኢዜአ አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.