Fana: At a Speed of Life!

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ቪዛ ዓለም አቀፍ አገልግሎት በጋራ ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከቪዛ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ጋር በሀዋላ፣ በዲጂታል ፋይናንስና በአዳዲስ የትብብር ዕድሎች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን ዓለማየሁ (ዶ/ር)÷ የኢትዮጵያ መንግስት በእኩልነትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የዲጂታላይዜሽን ትብብር እንዲጎለብት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል።

የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ስኬት ለማረጋገጥ በህግ ማዕቀፍ፣ በመሠረተ ልማቶችና በሰው ሀይል ግንባታ ላይ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የቪዛ ኢንክ የደቡብና ምስራቅ አፍሪካ ሪጅን ምክትል ፕሬዚዳንት ሚካኤል በርነር  በበኩላቸው÷ ዓለም አቀፍ የቪዛ አገልግሎትን በኢትዮጵያና በቀጣናው ሀገራት ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልፀዋል።

የቪዛ ክፍያ መፍትሄዎችን፣ ቴክኖሎጂዎችንና የዲጂታል ስነ-ምህዳርን በኢትዮጵያ ለማጎልበት እንደሚያስችል ገልጸው÷ ዓለም አቀፍ እና ክልላዊ ተሞክሮዎች እንደሚተገበሩም ጠቁመዋል።

ሁለቱ ወገኖች የመንግስት አገልግሎቶችን ዲጂታይዝ ለማድረግ፣ የፋይናንስ አካታችነትን ለማሳደግ እና  የገቢ አሰባሰብ ቅልጥፍናን በማሻሻል ረገድ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል፡፡

በተጨማሪ የኢትዮጵያን አጠቃላይ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ፣ የዲጂታል ስትራቴጂው የቅድሚያ ፕሮጀክቶችን እና የትግበራ እቅዶችን ለመደገፍና በጋራ ለመስራት ስምምነት ላይ መደረሱን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.