Fana: At a Speed of Life!

የካሊፎርኒያ ኢኮኖሚ ከዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ አራተኛዋ ሀገር ጃፓን በለጠ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ኢኮኖሚ ከዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገራት ተርታ በአራተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠችው ጃፓን መብለጡ ይፋ ሆነ።

ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) እና ዩኤስ ኢኮኖሚክ ትንተና ቢሮ በተገኘው መረጃ መሰረት በፈረንጆቹ 2024 የካሊፎርኒያ ግዛት 4 ነጥብ 1 ትሪሊየን ዶላር አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት አስመዝግባለች።

በዚህም የዓለም ግዙፍ ኢኮኖሚ ሀገራት ተርታ ከተሰለፉት መካከል በአራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችውን ጃፓንን መብለጥ ችላለች።

ካሊፎርኒያ በአሜሪካ ትልቁን የማኑፋክቸሪንግ እና የግብርና ምርት ድርሻ የምትይዝ ሲሆን፤ የዓለም የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ማዕከል እና የሀገሪቱ ሁለት ትላልቅ የባህር ወደቦች መገኛ እንዲሁም ግንባር ቀደም የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤት ነች።

የካሊፎርኒያ ገዢ ጋቪን ኒውሶም የተመዘገበውን ውጤት አድንቀው፤ ነገርግን የፌዴራል የንግድ ፖሊሲዎች የወደፊት እድገት ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ጃፓን እያሽቆለቆለ በመጣው የህዝብ ብዛት እና እርጅና ምክንያት የሰው ሀይል መቀነሱ እና የማህበራዊ እንክብካቤ ወጪዎች እየጨመሩ መምጣታቸው ኢኮኖሚዋን ጫና ውስጥ ከቶታል መባሉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

በዓለም የግዙፍ ኢኮኖሚ የደረጃ ሰንጠረዥ ውስጥ አሜሪካ ቀዳሚዋ ሀገር ስትሆን፤ ቻይና እና ጀርመን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።

ኢኮኖሚዋ በካሊፎርኒያ ግዛት የተበለጠው ጃፓን አራተኛዋ ሀገር ናት።

በሔለን ታደሰ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.