Fana: At a Speed of Life!

ጽንፈኛው ቡድን በመምህራን ላይ የሚያደርሰው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በጽኑ የሚወገዝ ነው – የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን በየጊዜው በመምህራን ላይ የሚያደርሰው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት በጽኑ የሚወገዝ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ገለጹ።

በክልሉ ተማሪዎች የመማር መብታቸው እንዲከበር ወላጆች እና የትምህርት ማኅበረሰቡ መታገል እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ማኅበሩ ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ እስከ ዩኒቨርሲቲ ድረስ ያሉትን አባላቱን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ እየተጋ ይገኛል፡፡

በተጨማሪ የመምህራን መብታቸውና የሙያ ክብራቸው ተጠብቆ እንዲሠሩ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ይሁን እንጂ የመምህራንን ሙያዊ ክብር ዝቅ የሚያደርግ ኢ-ሰብዓዊ ተግባር ሲፈጸም እንደሚስተዋል ጠቁመው፤ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን በመምህራን ላይ የሚፈጽማቸውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ለአብነት አንስተዋል፡፡

ይህም ማኅበሩ ድርጊቱን አጥብቆ እንደሚያወግዘው ገልጸው፤ ድርጊቱ ትምህርት ቤቶች ደኅንነታቸው የተረጋገጠ መሆን አለበት የሚለውን የተባበሩት መንግሥታት መርኅ በእጅጉ የጣሰ ነው ብለዋል።

በክልሉ አንዳንድ ቦታዎች የተቋረጠውን የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ወደ መደበኛ ሥራ እንዲመለስ ከሚመለከታቸው ጋር በኅብረት እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

መምህራን ሙያዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በሚያደርጉት ጥረት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ማድረስ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሲሉም አውግዘዋል፡፡

በክልሉ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚደርሰውን ተጽዕኖ በቅርብ እየተከታተልን ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ በማንኛውም ወቅት መምህራን ላይ የሚደርስ ጥቃትን አጥብቀን እንቃወማለን ብለዋል።

በክልሉ አጠቃላይ በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች መጠን ከ40 በመቶ እንደማይበልጥ ገልጸው፤ ጽንፈኛው ቡድን የመማር ማስተማር ሂደት ማስተጓጎሉ የማኅበረሰቡንና የክልሉን የትምህርት ሁኔታ ወደ ኋላ እንደሚጎትት አስረድተዋል፡፡

ትምህርት ቤቶች ያሉት በየቀበሌው በመሆኑ ወላጆችና የትምህርት ማኅበረሰቡ ተማሪዎች የመማር መብታቸው እንዲከበር እና መማር ማስተማሩ በተሟላ መልኩ እንዲካሄድ መምከር፣ መገሰጽ እንዲሁም መታገል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.