አየር ኃይል ወደ ዘመናዊ የአቪዬሽን ተቋም ደረጃ አድጓል- ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠንካራ ተቋማዊ ሪፎርም እየተገነባ ያለው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ወደ ተሟላ ዘመናዊ የአቪዬሽን ተቋም ደረጃ ማደጉን ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አስታወቁ፡፡
የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ፤ በመከላከያ አዛዥነት እና ስታፍ ኮሌጅ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ከሚገኙ የክፍለ ጦር አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡
ዋና አዛዡ በዚሁ ወቅት፤ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአመራሩ ጀምሮ እስከታችኛው አባላት ደረጃ ለለውጥ ዝግጁ ሆነው በመሥራታቸው ተቋሙ ወደ ተሟላ ዘመናዊ የአቪዬሽን ተቋም ደረጃ ማደጉን ገልፀዋል።
ውስጣዊ አንድነቱ የጠነከረ ብሎም ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚችል ሙያዊ አቅም ያለው ሠራዊት እንደ ተቋም መገንባቱን አንስተዋል፡፡
በ2022 ከአፍሪካ ተመራጭ የአቪዬሽን ተቋም ለማድረግ ከያዝናቸው ውጥኖች መካከል አንዳንዶቹ ቀድመው እየተሳኩ ነው ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
ጠንካራ ወታደራዊ መሪ ማለት በሰላም ጊዜ ሠራዊቱን ለውጊያ የሚያዘጋጅና በአነስተኛ ኪሳራ ትልቅ ድል የሚያመጣ መሆኑን ሲሊም ገልጸዋል፡፡
የክፍለ ጦር አመራሮችም የዘመኑን ወታደራዊ ሳይንስ እና ጥበብ መከተል እንዳለባቸው አሳስበው፤ የሚሰጣቸውን ተልዕኮ ያገናዘበ አቅም ደረጃ ለመድረስም ራሳቸውን ለማብቃት ሊተጉ ይገባል ብለዋል፡፡