የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚታይ ውጤት እያስመዘገበ ነው – አቶ ማሞ ምህረቱ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም ጠንካራ እና የሚታይ ውጤት እያስመዘገበ ነው ሲሉ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገለፁ።
ባንክ ገዥው በ2025 አይኤምኤፍ እና የዓለም ባንክ ስብሰባ ላይ፤ ኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ አስተዳደሯን ሙሉ በሙሉ ነፃ ማድረግ ላይ ትኩረት ያደረገ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማድረጓን አብራርተዋል፡፡
ማሻሻያው የተቀናጀ ሀገራዊ ጥረት፣ በረጅም ጊዜ መረጋጋት እና ዕድገት ላይ ያተኮረ እንጂ የምንዛሪ ለውጥ ብቻ እንዳልሆነ ገልጸው፤ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦትን ማቃለል፣ ያረጁ መመሪያዎችን ማስወገድ እና ግልጽነትን ማሳደግን ያካተተ ሙሉ ማሻሻያ መሆኑንም ገልጸዋል።
በማሻሻው ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት እና ከዚህም የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ መጠን ከፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ክምችት በሦስት እጥፍ በማሳደግ የግሉ ሴክተር ተደራሽነት እንዲሻሻል ማድረጉን ጠቅሰው፤ የውጭ ምንዛሪ ደንቦች ከ87 አስቸጋሪ መመሪያዎች ተጨምቆ በአንድ መመሪያ እንዲስተካከል መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡
ከፊስካል እና የገንዘብ ፖሊሲዎች ጀምሮ ማሻሻያዎቹ በጥንቃቄ የተቀመጡ መሆናቸውን አንስተው፤ ቀጣይነት ያለው የገበያ ክትትል አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ማሻሻያው በባንክ ህጎች ላይ የተደረጉ ለውጦች፣ ዘርፉን ለውጭ ውድድር መክፈት፣ የማዕከላዊ ባንክ ህግን ማሻሻል እና ለዋጋ መረጋጋት ቅድሚያ መስጠትን እንደሚያካትት ገልጸው፤ ይህም መንግስት ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትና መረጋጋትን ለማምጣት ቁርጠኛ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።
የዋጋ ግሽበትን መቀነስን በተመለከተ የተወሰደው ርምጃ የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፤ የማዕከላዊ ባንክ ዋና ዓላማ በኢትዮጵያ የዋጋ ግሽበትን መቀነስ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ እየተተገበረ ባለው ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ በመጋቢት ወር የዋጋ ግሽበትን ከ30 በመቶ ወደ 13 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፤ በሚቀጥለው የበጀት ዓመት የዋጋ ግሽበቱን 10 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስታወቁት፡፡
ደፋር እንቅስቃሴዎች አድርገን ጠንካራ ውጤቶችን እያየን ነው ያሉት የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ፤ ለቀጣይ እድገት ጠንካራ መሰረት በመገንባት ከፍተኛ የግል ካፒታልን መሳብ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ አመላክተዋል።
በሔለን ታደሰ