Fana: At a Speed of Life!

የቻይና አየር መንገዶች ወደ ኢትዮጵያ የበረራ አገልግሎት ሊሰጡ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሁለት የቻይና አየር መንገዶች በፈረንጆቹ 2025 መጨረሻ ወደ ኢትዮጵያ የበረራ አገልግሎት ለመጀመር ማቀዳቸውን አስታወቁ፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግሥቴ በቻይና ባለሀብቶች ከተያዙ አፍሪካን ወርልድ እና ሀይናን አየር መንገዶች የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

በዚሁ ወቅት ኩባንያዎቹ ወደ ኢትዮጵያ የበረራ አገልግሎት ለመጀመር ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸው፤ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በበኩላቸው የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ከኢትዮጵያ እና ቻይና የትብብር መስኮች አንዱ መሆኑን አስረድተው፤ በሀገራቱ የአየር አገልግሎት ስምምነት መሠረት ባለሥልጣኑ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

የበረራ አገልግሎት ለመጀመር የሚያስፈልጉ ዝርዝር መስፈርቶችን በተመለከተም ለኩባንያዎቹ ኃላፊዎች አስረድተዋል፡፡

ሁለቱ አየር መንገዶች ቅድመ ሁኔታዎቹን በማሟላት በተያዘው የፈረንጆቹ 2025 መጨረሻ በረራውን ለመጀመር ማቀዳቸውን የባለስልጣኑ መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.