ኢትዮጵያና ሞሮኮ በወታደራዊ ዘርፍ በትብብር መሥራት በሚችሉበት ጉዳይ ላይ መከሩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ሞሮኮ በወታደራዊ ዘርፍ በትብብር ለመሥራት በሚያስችሏቸው ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ባሬድ ከተማራ ልዑክ ጋር ተወያይተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ እና በራባት የተካሄደው የከፍተኛ ደረጃ ወታደራዊ ልዑካን ምክክር፤ ሁለቱ ሀገሮች በትብብር ለመሥራት የሚያስችሉ ጉዳዮችን እንዲፈትሹ ዕድል መፍጠሩን ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጠቅሰዋል፡፡
የሞሮኮ ሮያል ጦር ኃይል ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄነራል ሞሐመድ ባሬድ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃነት ምልክት መሆኗን ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ ትብብርም ለአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ለምናበረክተው አስተዋፅኦ የጎላ ሚና ይኖረዋል ማለታቸውን የመከላከያ ሠራዊት ማኅበራዊ ትሥሥር ገጽ መረጃ አመላክቷል፡፡
ከሞሮኮ ወታደራዊ ተቋማት በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሳይበር ደኅንነት፣ በአየር ኃይልና በባሕር ኃይል ኢትዮጵያ የምትወስደው ተሞክሮ እንዳለም ተጠቁሟል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ላይ በኢንዱስትሪ እያሳየች ካለው እምርታ አንፃር ሀገራቱ በትብብር እንደሚሠሩና መጪውን ሁኔታ ያገናዘበ ልምድና ተሞክሮ በመለዋወጥ በቀጣናው በሚኖሩ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችላቸውን ፍሬያማ ምክክር ማድረጋቸው ተነስቷል፡፡
ሁለቱ ሀገራት በቀጣይ የመግባቢያ ስምምነት እንደሚፈራረሙ የተገለጸ ሲሆን፤ ውይይቱን ተከትሎ የልዑካን ቡድኑ አባላት በሆሚቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪና በአየር ኃይል እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ጎብኝቷል፡፡