Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ትብብር ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ማክታር ዲዮፕ ገለጹ፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ ስብሰባ ጎን ለጎን ከዋና ዳይሬክተሩ ጋር ተወያይተዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፥ ተቋማቸው ለኢትዮጵያ የግልና የመንግስት አጋርነት ልማት፣ ለቴሌኮም ዘርፍ፣ ለግብርና እንዲሁም ለአውሮፕላን ማረፊያዎች ልማት ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ሚኒስትሩ በተመሳሳይ ከኩዌት ፈንድ ተጠባባቂ ዳይሬክተር ዋሊድ አል-ባሃር ጋር የተወያዩ ሲሆን፥ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የልማት ትኩረቶችና በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።

ማሻሻያው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ገበያ መር ስርዓት የሚያሸጋግርና የግሉን ዘርፍ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንደሚያሳድግ ገልጸው፥ የኩዌት ፈንድ መሰረተ ልማትን ጨምሮ ለተመረጡ ፕሮጀክቶች ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

ዳይሬክተሩ በበኩላቸው፥ ፈንዱ የኢትዮጵያን ቁልፍ የመሰረተ ልማትና ወሳኝ የልማት ፕሮጀክቶችን በመደገፍ ያለውን ትብብር ለማጠናከር ቁርጠኛ መሆኑን መናገራቸውን በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመልክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.