የሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል ልዑካን ኢትዮጵያ የገነባችውን የድሮን ቴክኖሎጂ አቅም አደነቁ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 17፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ የሚገኘው የሞሮኮ የሮያል ጦር ኃይል የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያ የገነባችውን የድሮን ቴክኖሎጂ አቅም አደንቋል፡፡
በጦር ኃይሉ ኢንስፔክተር ጄኔራልና የደቡባዊ ዞን ጦር አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ በሪድ የተመራው የልዑካን ቡድን የስካይ ዊን ኤሮናቲክስ ኢንዱስትሪንና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትን ጎብኝቷል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት ኢትዮጵያ በድሮን ቴክኖሎጂና ምርት በደረሰችበት የላቀ ደረጃ መደነቃቸውን ገልጸው፥ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር በጸጥታና ደኅንነት ዘርፎች የሁለትዮሽ ግንኙነቷን ለማጠናክር እንደምትሰራ አረጋግጠዋል፡፡
ኢትዮጵያ በድሮን ቴክኖሎጂ የምታከናውናቸው ተግባራትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ብሔራዊ ደኅንነትንና ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ረገድ በርካታ ፋይዳዎች እንዳሉትም ልዑካኑ ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪው የድሮን ምርት የሀገርን ድንበር ለመጠበቅና ለመቆጣጠር፣ ለልዩ ኃይል ኦፕሬሽንና ለሌሎች ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ጠቀሜታ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡
የሁለቱ ሀገራት የመረጃና የደኅንነት ተቋማት በተለያዩ መስኮች በትብብር ሲሰሩ መቆየታቸውን ተገልጿል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል ሲሳይ ቶላ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በጉብኝት መርሐ-ግብሩ መሳተፋቸውን አገልግሎቱ ለፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በላከው መረጃ ጠቁሟል፡፡