የብልጽግና ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ተጠናቋል።
የስብሰባውን መጠናቀቅ ተከትሎ ፓርቲው ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦
ከብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 17 እስከ 18/ 2017 ዓም መደበኛ ስብሰባውን በአዲስ አበባ አካሂዷል፡፡ በዚህ ስብሰባም የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች በዝርዝር ተመልክቷል፡፡ ኢትዮጵያ በ2018 ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብርሃን ለመሻገር፤ በ2023 የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለመሆን፤ በ2040 ደግሞ ዓለም አቀፍ የብልጽግና አርአያ ለመሆን ያስቀመጠችው ርእይ እንደሚሳካ የሚያረጋግጡ የስኬት ፍንጮች መታየታቸውን የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው አረጋግጧል፡፡ እነዚህ የስኬት ፍንጮች የያዝነው ፍኖተ ብልጽግና ትክክል መሆኑን አመላክተውናል፡፡
ከብልፅግና ፓርቲ ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ በኋላ አያሌ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች ተመዝግበዋል፡፡ ከተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በየደረጃው የሚደረገው ምክክርና ትብብር በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ወደ አዲስ ምእራፍ ገብቷል፡፡ ከአንድ ክልል በስተቀር፣ ለሀገራዊ ምክክር አጀንዳ የማሰባሰብ ምእራፍ በሁሉም ክልሎች ተጠናቅቋል፡፡ በሀገሪቱ የጸጥታ ችግር በነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎችም ሰላም እየሰፈነ ነው፡፡ መንግስት በተደጋጋሚ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ እጅ የሚሰጡና ወደ ሰላም ድርድር የሚመጡ ታጣቂዎች ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየጨመረ ይገኛል፡፡ የመንግሥት ሕግ የማስከበርና የማድረግ ዐቅም እየጎለበተ መጥቷል፡፡ ከሶማሊያ ጋር ተፈጥሮ የነበረው ውዝግብ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ተፈትቷል፡፡ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንዲኖራት የተያዘው አቋም ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነቱ እየጨመረ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነት ከመሻሻሉም በላይ የሚደረግላት ድጋፍ እያደገ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ መድረክ የኢትዮጵያ ተፈላጊነት ጨምሯል፡፡ የዲፕሎማሲ ግንኙነቷም በሁሉም አቅጣጫ ከፍ ብሏል፡፡
እስከአሁን ያለው አፈፃፀም የሚያሳየው በያዝነው አመት አጠቃላይ ኢኮኖሚው በታቀደው መሠረት በ8.4 በመቶ የሚያድግ መሆኑን የሥራ አስፈጻሚው ገምግሟል፡፡ በዘርፍ ደረጃ ደግሞ ግብርና በ6.1 በመቶ፣ ኢንዱስትሪ በ12.8 በመቶ፣ ማኑፋክቸሪንግ በ12.0 በመቶ፣ ኮንስትራክሽን በ12.3 በመቶ፣ አገልግሎት ደግሞ በ7.1 በመቶ የሚያድጉ መሆናቸው ተገምግሟል፡፡ ያለፉት 9 ወራት ጠቅላላ የመንግሥት ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት አንጻር የ134 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ የውጭ ብድር ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ወደ 13.7 በመቶ ወርዷል፡፡ ወደ ውጭ ገበያ የሚቀርቡት ስድስት ዋና ዋና ምርቶች፣ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸሩ ከ82 በመቶ እስከ 386 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ በስንዴ፣ በሩዝ፣ በቡና፣ በሻሂ ቅጠል እና በፍራፍሬ ምርቶች በአፍሪካ ቀዳሚ ሆኖ ለመውጣት እየተደረገ ያለው ትግል ፍሬ እያፈራ መሆኑን አይተናል፡፡
ውድ የብልፅግና አመራሮች፣ የብልፅግና አባላትና መላው ሕዝባችን፣
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዝቅተኛ ኑሮ በሚኖሩ ወገኖች ላይ ጫና እንዳያሳድር አስፈላጊ የሆኑና የታቀዱ የድጋፍ መርሐ ግብሮች መከናወናቸውንም የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው መርምሯል፡፡ ለማዳበሪያ 62 ቢልዮን ብር፣ ለሴፍቲኔት 41.2 ቢልዮን ብር፣ ለነዳጅ 60 ቢልዮን ብር፣ ለመድኃኒት 3.5 ቢልዮን ብር፣ ለምግብ ዘይት 6.1 ቢልዮን ብር፣ እንዲሁም ለደመወዝ 38.4 ቢልዮን ብር ድጎማ ተደርጓል፡፡ ባለፉት 9 ወራት ብቻ 344,790 የውጭ ሀገር ሕጋዊ የሥራ ዕድሎች እና ከ3 ሚልዮን በላይ የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል፡፡ የርቀት የሥራ ዕድሎች ቁጥርም እየጨመረ መምጣቱ ታይቷል፡፡
የመንግሥት የልማት ተቋማትን በአዲስ አስተሳሰብና በአዲስ መንገድ መልሶ ለማደራጀትና ለመምራት መቻሉ፣ እያስገኘው ያለው ውጤት ለሌሎች አርአያ የሚሆን እንደሆነ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አሁን ያለው ጠቅላላ ገቢ 1.5 ትሪልዮን መድረሱ ታይቷል፡፡ ከባለፈው ዓመት የ9 ወራት አፈጻጸም አንጻር የዘንድሮ ገቢው የ86 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱም ተረጋግጧል፡፡ ይሄም መንግሥት የሀገርን ሀብት ለማወቅ፣ ዐውቆም በሚገባ ለማስተዳደር፣ አስተዳድሮም ወረት ለማከማቸት የተከተለው መርሕ ትክክል መሆኑን አረጋግጧል፡፡
የውጭ ምንዛሬ ክምችት ዕድገት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ 9 ወራት ጋር ሲነጻጸር የ203.99 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ ከ3 ትሪልየን በላይ ተሻግሯል፡፡ የ9 ወራት የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከ5 ቢልዮን ዶላር በላይ ሲሆን፣ ይሄም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ150.39 በመቶ ዕድገት አምጥቷል፡፡ ባለፉት ስምንት ወራት 473.9 ቢልዮን ብር ብድር ከንግድ ባንኮች ተለቅቋል፡፡ ይሄም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ አንጻር በ61.9 በመቶ ከፍ ይላል፡፡ ከዚህ ብድር ውስጥም 76.6 በመቶ ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ ነው፡፡ ለግሉ ዘርፍ የበለጠ ብድር መሰጠቱ፣ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ተገቢውን ሚና እንዲጫወት ያስቀመጥነው ፖሊሲ በተግባር እየተገለጠ መሆኑን አመላካች ነው፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ን ለማሳካት የጀመርናቸው ሁሉን አቀፍ ጥረቶች ፍሬያቸው እየጎመራ ነው፡፡ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች 50.2 ሚልዮን፣ የሞባይል ተጠቃሚዎችም 86.6 ሚልዮን ደርሰዋል፡፡ የቴሌ ብር ደንበኞችም ከ52.56 ሚሊዮን በላይ ናቸው፡፡ ዲጂታል ፋይናንስ፣ የኅብረተሰቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለኢኮኖሚው መሣለጥ ጉልህ ድርሻ እያበረከተ ነው፡፡ ባለፉት 9 ወራት በዲጂታል መንገዶች 7.73 ቢልዮን ብር ተቆጥቧል፡፡ 26.77 ቢልዮን ብር በዲጂታል በኩል ብድር ተሰጠ ሲሆን፣ የ12.51 ትሪሊዮን ብር ግብይት ደግሞ በዚሁ መንገድ ተከናውኗል፡፡
ዋና ዋና ፕሮጀክቶችን በጊዜና በተገቢ ደረጃ ለማጠናቀቅ የተሰጠው አቅጣጫ ብዙዎችን ለፍጻሜ እያበቃቸው ነው፡፡ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ አፈጻጸም 98.66 በመቶ ደርሷል፡፡ የኮይሻ፣ አይሻና አሰላ የኃይል ማመንጫዎች በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት እየተጓዙ መሆናቸው ተገምግሟል፡፡ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ግንባታም የኢትዮጵያን ነገ ታሳቢ ባደረገ መልኩ የቅድመ ዝግጅት ምእራፉ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የኮሪደር ልማት በአዲስ አበባ በ8 ኮሪደሮች እና በመላው ኢትዮጵያ በ65 ከተሞች እየተከናወነ መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ ብዙዎቹ የመስኖ ግድቦች ወደ ፍጻሜያቸው እየደረሱ ናቸው፡፡ ከዘጠኙ የመስኖ ግድቦች ውስጥ ስድስቱ አፈጻጸማቸው ከ75 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡
“ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ቃል ከ82 ቢልዮን ብር በላይ ድጋፍ የተሰበሰበ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 6815 ትምህርት ቤቶች በመላ ሀገሪቱ ተገንብተዋል፡፡ የነባር ትምህርት ቤቶችን ዐቅም ለማሻሻል እና በግጭት የተጎዱትን ለመጠገን የተደረገው ጥረት በትውልድ ላይ ለሚሠራው ሥራ መሠረት የሚጥል መሆኑ ታይቷል፡፡ የወላድ እናቶችን እና የጨቅላ ሕጻናትን ሞት በመቀነስ ረገድ የተሻለ ውጤት መመዝገቡም ታይቷል፡፡
በኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎችና የስፖርት ሥፍራዎች በቁጥርም፣ በዓይነትም እያደጉ መጥተዋል፡፡ በተለያዩ ከተሞች በመገንባት ላይ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ስታዲየሞች በመጠናቀቂያ ምእራፍ ላይ ናቸው፡፡ ይሄም ኢትዮጵያ ታላላቅ አፍሪካዊ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ለያዘችው ዕቅድ መሳካት ወሳኝ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ኩነቶችን ለማስተናገድ ያላት መሠረተ ልማት እና የመስተንግዶ ዐቅም እያደገ ይገኛል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ66 በላይ ዓለም አቀፍ ኩነቶች በሀገራችን ተደርገዋል፡፡ በቱሪስት ፍሰት ጭማሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሀገር በመሆን ላይ ነን፡፡ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊ፣ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ ጸጋዎች አውጥተን ማሳየት ከቻልን፣ በቱሪዝም መስክ የቀዳሚነት ሚና መጫወት እንደምንችል ጅምሮቹ ያሳያሉ፡፡
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተከናወኑ ተግባራት አምራችነትን በማበረታታት፣ ሥራ ያቆሙ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ሥራ በማስገባት፣ ገቢ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት፣ የሀገር ውስጥ ገቢን በማሰባሰብ፣ ወጪ ምርቶችን በብዛት በማምረት፣ ከአንድ ጊዜ በላይ መሬትን ደጋግሞ በማረስ፣ ሪፎርሞችን በየዘርፋቸው አግባብ በመተግበር፣ የተመዘገቡ ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ የተነሣ ራስን የመቻል ተነሣሽነት ጨምሯል፡፡ ዘጠኝ ክልሎች ሰብአዊ ድጋፍን በራሳቸው ዐቅም ከመሸፈናቸውም በላይ የሰብአዊ ድጋፍ ፈላጊዎች ቁጥርም ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ በ86 በመቶ ቀንሷል፡፡ ሂደቱ ተረጂነትን መጸየፍና አምራችነትን ባህል ማድረግ በሀገራችን ሥር እየያዘ መሆኑን አመላካች ነው፡፡
ውድ የብልፅግና አመራሮች፣ የብልፅግና አባላትና መላው ሕዝባችን፣
እነዚህ ስኬቶች የጉዟችን መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ አይደሉም፡፡ ማበረታቻዎች እንጂ ፍጻሜዎች አይደሉም፡፡ ስኬቶቹ መንገዳችን ትክክል መሆኑን የሚያሳዩ የተራራ ላይ መብራቶች ናቸው፡፡ ለበለጠ ሥራ የሚያነሣሡ፣ ለበለጠ ወኔ የሚቀሰቅሱ፣ የጠለቀ ቁጭት የሚቆሰቁሱ ናቸው፡፡
በሠራናቸው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የጸጥታ ተቋማት ሪፎርሞች ሀገራችን ከነበረባት የህልውና አደጋ ወጥታ ወደ አስተማማኝ ህልውና እየተሻገረች ነው። ሪፎርሙ የነበረውን የህልውና ሥጋት መቀልበስ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገርን ህልውና ለመጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝ ዐቅም ፈጥሯል፡፡ ይሄም በተቃራኒው መንግሥትን በኃይል ለመጣል የነበረውን ፍላጎት አምክኗል፡፡
በተደረጉ ሀገር በቀል ማሻሻያዎች፣ በተፈጠረው ዐቅም እና ዝግጁነት ኢኮኖሚያችን ወደ ተሟላ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ ገብቷል፡፡ ይሄ ደግሞ የኢኮኖሚ ሂደታችንን እና የብልጽግና ጉዟችንን የሚቀይር አዲስ ምእራፍ ፈጥሯል። የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ እና የባሕር በር ጉዳይ በቀጣናችን የአጀንዳ የበላይነት እንድንፈጥር አስችሎናል፡፡ በዚህም የተነሣ ሀገራችንን ከተከላካይነት ወደ ተጽዕኖ ፈጣሪነት አሸጋግሯታል። በመሆኑም ለውጡ ከመተከል ወደ ማንሠራራት ተራምዷል ማለት ይቻላል።
መንግሥት የፈጠረው ዐቅም፣ የፀረ ለውጥ ኃይሉ መዳከም እና ዓለም አቀፍ ለውጡ የኢትዮጵያን ሪፎርም ለማሳካት የተሻለ ዕድል የሚሰጥ ነው፡፡ መንግሥትን በኃይል ለመጣልና ፍላጎትን በጉልበት ለማሳካት የሚደረገው መፍጨርጨር ውጤት እንደማያስገኝ ሀገራዊ እውነት እየሆነ ነው፡፡ በየጊዜው ወደ ሰላም የሚመጡት ታጣቂዎች ቁጥር መጨመርም ይሄንን ያመለክታል፡፡
በአንድ በኩል እነዚህን ስኬቶች ይበልጥ ማስፋትና ማጽናት አለብን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ራሳችንን ከመሐል ዘመን ወጥመድ መጠበቅ ይገባናል፡፡ የመሐል ዘመን ወጥመድ፣ አንድ ሀገር ከፖለቲካ ሥርዓት ሽግግር በመውጣት፣ ወደ ቀጣዩ የማጽናት ምእራፍ ከመድረሷ በፊት፣ በሚገኘው የመሐል ዘመን፣ በስኬቶች ረክቶና ተዘናግቶ የመቀመጥ አባዜ ነው፡፡ ከፖለቲካ ሽግግር በመውጣትና የጸና ሥርዓትን በመትከል መካከል የሚገኝ ፈታኝ ዘመን ነው፡፡
የሀገራችን ኢኮኖሚ በማደግ ላይ ያለ እንጂ በሚፈለገው መጠን ያደገ አይደለም፡፡ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በከተማ ልማት፣ በወጪ ምርቶች፣ በማዕድን፣ በአገልግሎት ዘርፍ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ፣ ወዘተ. ያየናቸው ለውጦች ብንሠራ የት እንደምንደርስ አመላካቾች ናቸው፡፡ ከግባችን መድረሳችንን ግን አያበሥሩም፡፡ የፖለቲካ ባህላችን እየተለወጠ ነው፤ ነገር ግን የሠለጠነ የፖለቲካ ባህል ገና አልገነባንም፡፡ የጸጥታ ተቋሞቻችን እየዘመኑና እየደረጁ ናቸው፤ ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ልክ ገና አልደረሱም፡፡ የፖለቲካ ፍላጎትን በኃይል የማስፈጸም አካሄድ ፋሽኑ እያለፈበት መጥቷል፡፡ ነገር ግን ገና ከፖለቲካና ከማኅበራዊ ባህላችን ተፍቆ አልጠፋም፡፡ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ገና በጅምር ላይ ነው፡፡ ዕዳችን ቢቃለልም ገና ከጫንቃችን ፈጽሞ አልወረደም፡፡ የዋጋ ግሽበትን ብንቋቋመውም፣ የኑሮ ውድነትን ግን በተገቢው መንገድ ገና አላቃለልነውም፡፡
በመሆኑም ከስኬት ማማ ላይ የደረስን መስሎን፣ በመሐል ዘመን ወጥመድ እንዳንያዝ አመራሮችና አባላት ነቅተው እንዲታገሉ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በአጽንዖት ያሳስባል፡፡
የመሐል ዘመን ወጥመድ በዋናነት የሚከሠተው በውጤት በመዘናጋት፣ ችግርን በመላመድ፣ ሀገራዊ ዕይታን ትቶ በጎጥ ውስጥ በማደር እና የሕዝብን ችግሮች በጊዜያቸውና በልካቸው ባለመፍታት ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህ ችግሮች የመሐል ዘመን ወጥመድን እንዳያመጡብን በአመራሩና በአባላቱ ዘንድ ትግል ሊደረግባቸው ይገባል ፡፡
ውድ የብልፅግና አመራሮች፣ የብልፅግና አባላትና መላው ሕዝባችን፣
የተዛባ ትርክት እንዳይፈጠር የብሔራዊ ዐርበኝነት ትርክትን በሚገባ ማሥረጽ ይጠበቅብናል፡፡ የሕዝብን ጥያቄዎች በየደረጃው መፍታት አለብን፡፡ ምርትና ምርታማነትን ከፍ በማድረግ የኑሮ ውድነትን የሚያቃልሉ ሥራዎችን መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ የተጀመሩ ኢኒሼቲቮችን የሕዝብ ርካታ በሚፈጥሩ መልኩ ወደ ውጤት ማድረስ አለብን፡፡ ከጠላቶቻችንን ላይ የመሣሪያም የትርክትም ትጥቅ ማስፈታት ይገባል፡፡ ለጠላት ተጋላጭነትን ሊፈጥሩ የሚችሉ አሠራሮችን ማረም ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው፡፡ የአመራር ሥምሪትን መፈተሽና ማጥራት መንገዳችንን የበለጠ ምቹ ያደርገዋል፡፡ ትጋትና ቁርጠኝነትን መጨመር፣ መናበብንና ቅንጅትን ማሣለጥ አለብን፡፡
ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚፈጥሩ፣ ገዥ ትርክትን የሚያሠርጹ፣ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን የሚያስከብሩ እና የኢትዮጵያን ብልጽግና የሚያረጋግጡ ተግባራትን ባለማሰለስ በየአካባቢያችን ተግተን ማከናወን ያስፈልገናል፡፡
የክረምት የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን በተገቢ ዕቅድ እና ቅንጅት መርተን ለውጤት ማብቃት ይገባናል፡፡ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር በዚህ ዓመት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት ሕዝቡን የማትጋትና የማሳተፍ ሥራ ከአሁኑ መጀመር አለበት፡፡ ለመኸር የእርሻ ሥራዎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችና ማሽነሪዎች በተገቢ ቦታና ጊዜ እንዲደርሱ የአመራር ሚናችንን እንወጣ፡፡ አንድም መሬት ጦም በማያድርበት ሁኔታ የግብርና ሥራዎች እንዲከናወኑ እናድርግ፡፡
በአጠቃላይ፣ በሰላማዊ እና በሠለጠነ መንገድ ልዩነቶቻችን በመፍታት፣ የጀመርናቸው ሪፎርሞች በማሳካት፣ የገጠሙንን ፈተናዎች በጽናት በማለፍ፣ ተግዳሮቶቻችንን በመጋፈጥና በማሸነፍ፣ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን እንድናደርግ፣ የብልፅግና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለብልፅግና ፓርቲ አመራርና አባላት፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች እና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ ያቀርባል፡፡
የብልፅግና ፓርቲ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
ሚያዝያ 18/ 2017፤ አዲስ አበባ