Fana: At a Speed of Life!

የብድር አያያዝ ውሎችና ሁኔታዎችን በተመለከተ ግልፅ አሰራርን የበለጠ ማጎልበት ይገባል – ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በተበዳሪው ሀገር እና በአበዳሪዎች ኮሚቴ መካከል የብድር አያያዝ ውሎችና ሁኔታዎችን ይፋ በማድረግ ግልፅ አሰራርን የበለጠ ማጎልበት እንደሚገባ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በዋሽንግተን ዲሲ አየተካሄደ ካለው የዓለም ባንክ ግሩፕ እና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ዓመታዊ የፀደይ ወቅት ስብሰባ ጎን ለጎን በዓለም አቀፉ የሀገራት የዕዳ ውይይት ላይ ተሳትፏል።

በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጆርጂዬቫ፣ በዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ እና በወቅቱ የቡድን 20 ሊቀመንበር በሆነችው ደቡብ አፍሪካ በተመራው ስብሰባ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ የዕዳ ሽግሽግ ሂደት የሚገኝበትን ደረጃ ገምግሟል።

በመድረኩ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)÷ የዕዳ ማዕቀፉ ፋይዳ ወሳኝ እንደሆነ እና ይህም በዛምቢያ፣ ጋና እና አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ የተደረጉት የተሳኩ የዕዳ ሽግሽግ ጥረቶች ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተበዳሪው ሀገር እና በአበዳሪዎች ኮሚቴ መካከል ባለው የመርህ ስምምነት መሰረት የብድር አያያዝ ውሎችና ሁኔታዎችን ይፋ በማድረግ ግልፅ አሰራርን የበለጠ ማጎልበት እንደሚገባም አመልክተዋል።

ከአበዳሪ ሀገራት ጋር የመርህ እና የሁለትዮሽ ስምምነት እንዲሁም የመግባቢያ ሰነዶችን በመፈራረም ፈጣንና ቀልጣፋ ሂደት በማመቻቸት አላስፈላጊ መዘግየቶችን መቀነስ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ መጋቢት 2025 ከአበዳሪዎች ጋር በመርህ ደረጃ መስማማቷ የሚታወስ ሲሆን÷ በፈረንጆቹ ሰኔ 2025 የመግባቢያ ሰነዱ ዝግጅት እንደሚጠናቀቅ የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.