በመዲናዋ ሰላምን በማጽናትና ወንጀልን በመከላከል ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸው ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ ሰላምን በማጽናትና ወንጀልን በመከላከል ረገድ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን የከተማ አስተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ።
የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮና የደንብ ማስከበር ባለስልጣን የ2017 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጻም ግምገማ እየተካሄደ ነው፡፡
የቢሮው ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በዚሁ ወቅት፥ ህብረተሰቡ የሰላም ዘብነቱን ሚና አጠናክሮ እንዲቀጥል በርካታ የሰላም መድረኮች መካሄዳቸውን ገልጸው፥ በዚህም ተጨባጫ ውጤቶች መገኘታቸውን አንስተዋል፡፡
በርካታ አዳዲስ አባላትን በመመልመል እና በማሰልጠን እንዲሰማሩ መደረጉን ያነሱት ኃላፊዋ፥ ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሰላምን የማስጠበቅ ተግባራትን በማከናወን የወንጀል ምጣኔን መቀነስና ሰላምን በአስተማማኝ ደረጃ ማጽናት ተችሏል ብለዋል።
የሚያውኩ ድርጊቶች የሚፈጸሙባቸው ቦታዎችን በጥናት በመለየት የእርምት እርምጃ መወሰዱን ገልጸው፥ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት ሳይኖራቸው ዋጋ በመጨመር የመልካም አስተዳደር ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይ አስፈላጊው እርምጃ መወሰዱንም ተናግረዋል።
በተመሳሳይ የከተማዋ የደንብ ማስከበር ባለስልጣን ከጎዳና ላይ ንግድ፣ ከኮሪደር ልማት እንዲሁም ከመሬት ወረራና ህገ ወጥ ግንባታዎች ጋር በተገናኘ የደምብ መተላለፍ የፈጸሙ አካላት እንዲቀጡ በግምገማ መድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡
በግምገማ መድረኩ የተቋማቱ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸምን በመገምገም የቀሪ ወራት የትኩረት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡