ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከልን መርቀው ከፈቱ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከልን በዛሬው ዕለት መርቀው ከፍተዋል፡፡
ከንቲባዋ ማዕከሉ በአርቲስት ዓለምፀሃይ ወዳጆ አስተባባሪነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 39 ሚሊየን ብር ድጋፍ በማድረግ እንዲሁም በርካታ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበት ውብ ሆኖ መታደሱን ገልጸዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ከተሰሩ ስራዎች ጎን ለጎን በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ቅርሶችን በማደስ ተጨማሪ ውበት እና የቱሪስት መስህብ ለማድረግ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውንም አመላክተዋል።
ለአብነትም በፒያሳ አካባቢ ያሉ የቅርስ ስፍራዎች ይዘታቸውን ሳይለቁ አቧራቸው ተራግፎ ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ታድሰው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ መደረጋቸውን አንስተዋል።
የባህልና የትምህርት ማዕከሉ ለከተማዋ ከሚሰጠው የቱሪስት መዳረሻነት በተጨማሪ ለኢትዮጵያ ተተኪ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያግዝ እንደሆነም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
የማዕከሉ ግንባታ ለአራት ዓመታት ያህል ሲከናወን መቆየቱም በዚህ ወቅት ተገልጿል፡፡
120 ዓመታትን ያስቆጠረው ቅርሱ ከአሁን ቀደም የቢትወደድ ኃይለጊዮርጊስ ወልደሚካኤል መኖሪያ ቤት የነበረ ሲሆን፥ የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት እንዲሁም ፍርድ ቤት በመሆን አገልግሏል፡፡
በፍቅርተ ከበደ