በአማራ ክልል ከ139 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ባለፉት 9 ወራት ከ139 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን የክልሉ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቋል።
የቢሮው ምክትል ቢሮ ኃላፊ ዮሐንስ አማረ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ269 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 1 ሺህ 898 አልሚዎች ፈቃድ መሰጠቱን ገልጸዋል።
ለአልሚዎቹ ፈቃድ የተሰጠው በተለያዩ የስራ ዘርፎች መሆኑን እና ከመሬት አቅርቦት ጋር በተያያዘ ከ46 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ሳይት ፕላን የመለየት ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል።
ከ27 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሆነው መሬት ከሦስተኛ ወገን ነፃ የማድረግ ስራ መሰራቱን የገለጹት አቶ ዮሐንስ÷ ከ7 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የሚሆነውን መሬት ደግሞ ለኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች የማስረከብ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
በሌላ በኩል 585 አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ640 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ የማስቀረት ስራ መሰራቱን እና 51 የሚደርሱ አምራች ኢንዱስትሪዎች ከ139 ሚሊየን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬን ማስገኘታቸውን አብራርተዋል።
758 የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት መደረጉን እና ከዚህ ውስጥ 344 የሚሆኑት አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርትና አገልግሎት መግባታቸውን ተናግረዋል።
ፈቃድ በተሰጠባቸው ፕሮጀክቶች ከ52 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩንም አመላክተዋል።
በምናለ አየነው