Fana: At a Speed of Life!

አቡነ ፍራንሲስ የዓለምን ህዝብ በቅንነትና በጎነት አገልግለዋል – ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ ለተገፉ ድምጽ፣ ቀን ለጎደለባቸው መከታ በመሆን የዓለምን ህዝብ በቅንነትና በጎነት አገልግለዋል ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ የመሥዋዕተ ቅዳሴ፣ ሥርዓተ ፍትሐትና የሐዘን መግለጫ ፊርማ የማኖር ሥነ ሥርዓት በልደታ ማርያም ካቶሊክ ካቴድራል ተካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴን ጨምሮ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ እንዲሁም የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማት አባቶችና የእምነቱ ተከታዮች ታድመዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ በዚሁ ወቅት፥ በአቡነ ፍራንሲስ ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው፥ ሰላም ላጡ ሀገራት ሁሉ ፈጥነው የሚደርሱ ታላቅ አባት እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት አቡነ ፍራንሲስ ቀን ለጎደለባቸው በጸሎት በማስታወስ ትልቅ አገልግሎት መስጠታቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፥ ዓለም ትልቅ ሰው ማጣቷን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ጸሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፥ ችግረኞችን ማገዝ፣ ስለ ሰላም መጸለይን ከአቡነ ፍራንሲስ ታሪክ መማር እንደሚገባ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ የቀብር ሥነ ሥርዓት በዛሬው ዕለት በሮም በሚገኘው ሳንታ ማሪያ ማጆሬ ቤተ-ክርስትያን ተፈጽሟል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.