አቶ አህመድ ሺዴ ከብሪታንያ ዓለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሺዴ ከብሪታንያ ዓለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ባሮንስ ቻፕማን ጋር ተወያይተዋል።
ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) እና የዓለም ባንክ ስብሰባ ጎን ለጎን ሚኒስትሮቹ ባደረጉት ውይይት በሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ዙሪያ መክረዋል።
አቶ አህመድ ሺዴ በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለው ሪፎርም ያስመዘገባቸውን ስኬቶች በተመለከተ ባደረጉት ገለጻ፥ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የብሪታኒያ ድጋፍ ወሳኝ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
ባሮንስ ቻፕማን በበኩላቸው በኢትዮጵያ የሪፎርም ስራዎች ያመጡትን ውጤት አድንቀው፤ ምቹ የቢዝነስ ከባቢ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት እና ኢትዮጵያ በቀጣናው ጠንካራ ትስስር እንዲፈጠር የምታከናውነውን ተግባር መንግስታቸው እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።
በውይይታቸውም ኢንቨስትመንት፣ ንግድና ሌሎች የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ጨምሮ የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር መስማማታቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።