የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መነሻና መድረሻውን መስቀል ዐደባባይ ያደረገው የ2017 ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድር ተካሄደ፡፡
የሩጫ ውድድሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፤ ውድድሩም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ 4ኛ ዓመት ዝግጅትን አስመልክቶ የተሰናዳ መሆኑ ተገልጿል።
በዝግጅቱ ላይ የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
አቶ መላኩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ጤናማና አምራች ዜጋ ለመፍጠር ስፖርት ከፍተኛ ሚና አለው፡፡
የሩጫው ዋና ዓላማ የሀገርን ምርት ለውጭው ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ መሆኑን አስረድተው፤ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያን ምርት ለብሰው ሲሮጡ በአትሌቲክሱ ያገኘነውን ድል በኢንዱስትሪውም መድገም እንደምንችል ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ወ/ሮ ሸዊት በበኩላቸው፤ የውጭ ምንዛሪን ለማዳን ዜጎች በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የስፖርት አልባሳትንና ሌሎች መስሪያ ቁሳቁሶችን ሊጠቀሙ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በሁለቱም ጾታ በቅደም ተከተል ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ ለወጡ ተወዳዳሪዎች፤ የ300 ሺህ፣ የ200 ሺህ እና የ100 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በውድድሩ የአምራች ኢንዱስትሪ ተዋናዮች፣ አጋር ድርጅቶች፣ ከ34 በላይ የአትሌቲክስ ክለቦችና መላው የአትሌቲክሱ ቤተሰቦች በአጠቃላይ ከ14 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል፡፡