Fana: At a Speed of Life!

የሠመራ የኮሪደር ልማትን በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ወጪ ከታኅሣስ 15 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በሠመራ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የፊታችን ሰኔ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው፡፡

የኮሪደር ልማቱ ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ ፓርኮች፣ ሙዚዬም እና ካፍቴሪያዎችን ያካተተ መሆኑን የሠመራ ሎግያ አሥተዳደር የከተማ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ ሀመዱ ኢሴ አሊ (ኢ/ር) ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ደረጃውን የጠበቀ አነስተኛ የእግር ኳስ ሜዳ፣ የሕጻናት መጫዋቻዎች፣ ከመሬት በታች የእግረኛ ሟቋረጫ ያለው ዐደባባይ፣ በዐደባባዩ ላይ 20 ሜትር የሚረዝም የአፋር ባህላዊ ጎራዴ (ጊሌ) መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

በሁለቱም ጎን ሦስት ሜትር የአስፋልት ማስፋፊያ እና የብስክሌት መንገድ፣ አምሥት ሜትር ስፋት ያለው የእግረኛ እና ለተለያየ አገልግሎት የሚውሉ መስመሮች ማካተቱን አብራርተዋል፡፡

ለአጠቃላይ ሥራውም በክልሉ መንግሥት የተሸፈነ 1 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር መመደቡን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ባለሃብቶችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ በቅርቡ ቴሌቶን ለማካሄድ መታሰቡን ጠቁመዋል፡፡

በዮሐንስ ደርበው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.