የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ረገድ አበረታች ውጤት መታየቱ ተመላከተ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከውጭ ስናስመጣቸው የነበሩ የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ደረጃ አበረታች ጅማሮ አይተናል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ፡፡
30ኛው የሜዲካል ላቦራቶሪ የሙያ ማኅበር ዓመታዊ ሳይንሳዊ ጉባዔና ዓለም አቀፍ የሜዲካል ላቦራቶሪ ባለሙያዎች ሳምንት “ላቦራቶሪ ሕይወት ያድናል!” በሚል መሪ ሐሳብ ተከብሯል፡፡
ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት፤ የላቦራቶሪ አገልግሎት በግልና በመንግሥት ተቋማት ቅንጅታዊ አሠራር ፈር ቀዳጅ ልምድ እንዳለው ጠቅሰው፤ የኮቪድ ወረርሽኝ የላቦራቶሪ አቅማችንን ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮልናል ብለዋል፡፡
ለዘርፉ ትኩረት መሰጠቱን አስታውቀው፤ አሁንም በሀገር አቀፍ ደረጃ የላቦራቶሪ አቅምን ለማሳደግ እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች ነው ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል፡፡
ከውጭ ስናስመጣቸው የነበሩ የሕክምና ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት ደረጃም አበረታች ጅማሮ አለ ነው ያሉት፡፡