Fana: At a Speed of Life!

10 ሺህ 600 ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ መቀበላቸው ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል 10 ሺህ 600 ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ መቀበላቸውን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቴ የሱፍ (ዶ/ር) አስታወቁ፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ በዘረፋ እና ግድያ ተግባር ላይ የተሰማራውን ፅንፈኛ ቡድን በመከታተል የተጠናከረ እርምጃ እየተወሰደ ነው፡፡

በዚህም በበርካታ አካባቢዎች መረጋጋት ተፈጥሮ መደበኛ እንቅስቃሴዎች መቀጠላቸውን ጠቅሰው፤ የመንግሥትን ጥሪ የተቀበሉ ታጣቂዎችም እጃቸውን ለመንግሥት እየሰጡ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በተያዘው ዓመት እስከ አሁን 10 ሺህ 600 ታጣቂዎች የመንግሥትን የሰላም ጥሪ መቀበላቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ከእነዚህ መካከል ከ3 ሺህ የሚልቁት የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውን እና ቀሪዎቹን ወደ ስልጠና ማዕከል ለማስገባት ዝግጅት መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል።

የሰላም አማራጭን ተከትለው ለሚመጡ ታጣቂዎች የመንግሥት እጅ አለመታጠፉን አመላክተው፤ የክልሉን ሰላም ለማወክ በሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ቡድን ላይ ግን እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.