መንግስት በፈጠራና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግስት በፈጠራ እና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
የትምህርት፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ እንዲሁም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴሮች ከአፍሪካ ብሬይንስ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት “ኢኖቬሽን አፍሪካ 2025” ጉባዔ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በጉባዔው የአፍሪካ ሀገራት የዘርፉ ሚኒስትሮች፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የትምህርት አጋር ድርጅቶች እና የግሉ ሴክተር ባለሃብቶች ተሳትፈዋል፡፡
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ÷ ቀጣዩን ትውልድ ለመገንባት ትምህርት፣ ቴክኖሎጂና ክህሎት ወሳኝ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ትምህርትና ክህሎትን ማዕከል በማድረግ በት/ቤት ግንባታና መሠረተ ልማት ማሻሻል፣ በዲጂታል ኔትዎርክ ግንባታ እንዲሁም በፈጠራና ክህሎት ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በበኩላቸው÷ አሁን ያለንበት የዓለም ሁኔታ በጣም የተወሳሰበ በመሆኑ መጪውን ትውልድና ወጣት በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በክህሎት ማዘጋጀት ይጠበቃል ብለዋል።
በትምህርት፣ በቴክኖሎጂና በክህሎት ዘርፍ የሚደረገው ውይይትም በትክክል ለአፍሪካ ለውጥ መሠረት የሚጣልበት ሊሆን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ለሦስት ቀናት በሚካሄደው ጉባዔ ከትምህርት፣ አይሲቲ እና ክህሎት ጋር የተያያዙ ወሳኝ አጀንዳዎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸውም የሚኒስቴሩ መረጃ አመላክቷል።