የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚፈታ ነው – አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በህዝብ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚፈታ መሆኑን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የምክር ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በመገኘት የተቋሙን የስራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል።
በጉብኝቱ ለምክር ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ስለማዕከሉ አገልግሎት አሰጣጥ ገለፃ ተደርጎላቸዋል።
አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በዚህ ወቅት÷ ከህዝብ ከሚነሱት ቅሬታዎችና ጥያቄዎች መካከል በየተቋማቱ የሚሰጡ አገልግሎት አና የመልካም አስተዳደር ችግር ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግስት የሚሰጡ አገልግሎቶች ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ወጪ ቆጣቢ እና የህዝብን ቅሬታ፣ ምልልስና ድካም የሚቀንሱ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
አገልግሎት አሰጣጥ ዘመናዊ፣ የተገልጋዮችን ቅሬታ የሚፈታ እንዲሁም ወጪን፣ ጊዜና እና ጉልበትን የሚቀንስ መሆኑን ያብራሩት አፈ ጉባኤው÷ ማዕከሉ የአገልግሎት አሰጣጥና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚፈታ ነው ብለዋል፡፡
የማዕከሉ አገልግሎት ዘመናዊ፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን የሚያስቀር፣ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ከህዝብ የሚነሳውን ቅሬታና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የሚፈታ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ለሀገር ትልቅ አስተዋፅኦ የሚሰጡ መሰል ተቋማትን በመገንባት ረገድ የበኩላቸውን ጥረት ያደረጉ አካላት ሊመሰገኑ እንደሚገባ እና ተቋማቱን በመደገፍና በማጠናከር ረገድ ሁሉም አካላት የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ምክር ቤቱም ማዕከሉን በህግ ማዕቀፍ፣ በክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም በህዝብ ውክልና ስራው ድጋፍ ያደርጋል ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ አመላክቷል፡፡