Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ እየተሳተፈች ነው

አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በብራዚል ሪዮ ዲ ጄኔሮ እየተካሄደ በሚገኘው የመጀመሪያው የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ እየተሳተፈች ነው፡፡

በመድረኩ ኢትዮጵያን በመወከል የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ባደረጉት ንግግር÷ ኢትዮጵያ ለብዝሃነትና የጋራ ደህንነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡

የዓለም አቀፍ አስተዳደር ተቋማት ብዝሃነት እና ባለብዙ ወገንተኝነትን በሚያጠናክር መልኩ መሻሻል እንዳለባቸው የገለጹት ሚኒትሩ እንደ አፍሪካ በማደግ ላይ የሚገኙ አህጉራት ፍትሃዊ ውክልና ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡

የብሪክስ አባል ሀገራት አሁን ላይ ያለውን ዓለም አቀፋዊ ውጥረት በመገንዘብ ለችግሮች ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ አማራጮች ለመፈለግ የሚያደርጉትን ጥረት አድንቀዋል፡፡

ጥረቶቹ የደቡብ ሀገራትን ደህንነት፣ ኢኮኖሚያዊ እና አጠቃላይ ጥቅሞችን በሚያረጋግጥ መልኩ መቃኘት እንዳለባቸውም አመላክተዋል፡፡

የብሪክስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ እስከ ሚያዝያ 29 እንደሚቆይ የተገለፀ ሲሆን÷ በቆይታው ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ከብሪክስ ሀገራት አቻዎቻቸው ጋር የጎንዮሽ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.