ጎንደር የኢትዮጵያውያን ሁሉ የታሪካችን አሻራ እና የማንነታችን መገለጫ ናት – አቶ አረጋ ከበደ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጎንደር የኢትዮጵያውያን ሁሉ የታሪካችን አሻራ እና የማንነታችን መገለጫ ናት ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡
“ኑ ጎንደርን እንሞሽር” በሚል መሪ ሐሳብ ለታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ዘርፈ ብዙ ልማት የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ሸራተን አዲስ ሆቴል እየተካሄደ ነው።
በገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ የክልሉ መንግስት ለጎንደር፣ ለባሕር ዳር እና ለደሴ ከተሞች የኮሪደር ልማት ሥራዎች ለእያንዳንዳቸው 100 ሚሊየን ብር ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክታቸውም÷ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ግን ጎንደርን አቧራዋን በማራገፍ ያላትን እምቅ የመበልጸግ ዕድል በመጠቀም ድምቀቷ የበለጠ እንዲታይ ጅምር ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
ለትውልድ የምናስረክባትን ውብ እና ማራኪ ከተማ ለመገንባት ቆርጠን ተነስተናል ያሉት አቶ አረጋ÷ ይህንን ለማድረግ ጊዜው አሁን እና ዛሬ መሆኑን ተናግረዋል።
አባቶቻችን ውብ አድርገው የሰጡንን፣ እስካሁን ግን አቧራ ለብሳ የቆየችውን ከተማ ውብ እና ማራኪ አድርጎ የመገንባቱን ኃላፊነት ወስደናል ሲሉም አመላክተዋል።
“ጎንደር ሕንጻ ብቻ አይደለም የተሸከመችው፤ ይልቁንም የማንነት መገለጫ አሻራዎችን አምቃ የያዛች ከተማ መሆኗን መግለጻቸውን አሚኮ ዘግቧል፡፡